ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ መርሐግብር ነገ ምሽት ይካሄዳል

በዲኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ የተገለፀው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ መርሐግብር ነገ አመሻሽ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል ይካሄዳል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን ባሳለፍነው ዓርብ መጠናቀቁ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ የመዝጊያ መርሐግብሩ ነገ ምሽት ከ12:00 ጀምሮ በሸራትን አዲስ ሆቴል ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የክለብ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚያከናውን ይሆናል። በዲኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በሚያገኘው በዚህ ፕሮግራም ላይ ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ አሰልጣኝ ፣ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ፣ ኮከብ ግብጠባቂ እንዲሁም የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ጨምሮ ለመጀመርያ ጊዜ በሚከናወኑ ሌሎች ዘርፎች የኮከብ ሽልማቶች ይበረከታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዕለቱም በየደረጃው ከአንድ እስከ አስራ ሦስተኛ ደረጃ ለወጡ ክለቦች የገንዘብ ርክክብ የሚካሄድ ሲሆን ለውድድሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፆኦ ላደረጉ ተቋማት የዕውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም የሚካሄድ ይሆናል።

ለውድድሩ አሸናፊ ለሆነው ፋሲል ከነማ እስካሁን ከጊዜያዊ ዋንጫው ውጭ በልዩ ዲዛይን ከደቡብ አፍሪካ ይመጣል የተባለው ዋንጫ ሀገር ውስጥ ያልገባ ሲሆን ምን አልባት ነገ ከደረሰ በዚሁ ዕለት የሚሰጥ ይሆናል። ለኮከቦቹ በየደረጃው ከሚሰጠው ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ባለፈ የተለየ ትውስታ የሚፈጥር ሽልማት እንደሚበረከትም ሰምተናል።