የትግራይ ክልል ክለቦችን በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሀሳብ ሰጥተዋል

በወቅታዊ የሀገራዊ ጉዳይ ከትናንት በስትያ በተጠናቀቀው የዘንድሮ ውድድር ላይ ያልተሳተፉትን ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦችን የቀጣይ ዓመት ተሳትፎ በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የበላይ አካል የሆነው አክሲዮን ማኅበሩ ከአባላቱ (ክለቦች) ጋር በካፒታል ሆቴል ውይይቱን አካሂዷል። በስፍራው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራም የጠራ ውሳኔ ባልተሰጠበት የሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች የቀጣይ ዓመት ተሳትፎን በተመለከተ ሀሳብ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንቱም በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የሰጡት ማብራሪያ የሚከተለው ነው።

“የትግራይ ክልል ክለቦች በቀጣይ ፕሪምየር ሊግ ላይ ካልተሳተፉ ወርደው ወደ ሱፐር ሊግ አልያም አንደኛ ሊግ አይደለም የሚያመሩት። ከታችኛው (ክልል ሻምፒዮና) ነው የሚጀምሩት። ሊግ ካምፓኒው እንዲህ ቢሆን ብሎ ያስቀመጠው ነገር አለ። ይሄንን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በደንብ የሚያየው ይሆናል። እኛ ስልጣን ለመውሰድ አንሯሯጥም። የጋራ ቤት ነው የምንሰራው። ግን እንደዚህ አይነት ውሳኔ ለመወሰን ባለቤቱን ማናገር አለብን። የምናስተዳድረው እኛ አለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ ማክሰኞ የሦስቱንም ክለብ ፕሬዝዳንቶች፣ የክልሉን እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የክልሉን ስፖርት ኮሚሽን ጠርተናል። ጉዳዩንም እየተነጋገርንበት ነው። እኛ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተናል። በአጭር ጊዜም ተወያይተን የሊግ ካምፓኒው ቀነ ገደብ እስካስቀመጠበት ሐምሌ 15 ሥራችንን ጨርሰን እናስረክባችኋለን። ስለዚህ አታስቡ። ጉዳዩን በደንብ እና በትኩረት እየተከታተልን ስለሆነ። በአጠቃላይ የሚነሳው ነገር የጋራ ጉዳይ ስለሆነ ለመፍታት በጣም ዝግጁ ነን። ማክሰኞ ጠዋት ከተነጋገርን በኋላም በአንድ እና በሁለት ቀን ውስጥ የፌዴሬሽኑ አመራር ተሰብስቦ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል። የምንሰጠው ውሳኔ ግን የጎጠኝነት መንፈስ የሚነሳበት እንዳይሆን።”