ፋሲል ከነማ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነትን ፈፅሟል

የፋሲል ከነማ ክለብ ከሂውማን ብሪጅ ኢትዮጵያ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት መፈፀሙን ክለቡ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ2013 ሻምፒዮን የሆነው ፋሲል ከነማ ራሱን ለማጠናከር ብሎም ለክለቡ የሚሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሮችን በተለያዩ ቀናት እያደረገ ይገኛል፡፡ ቡድኑ በተሻለ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ከሚያደርገው የገቢ ማሰባሰብ ባሻገር በተሻለ የትጥቅ እና መሰል አቅርቦት ለቀጣዮቹ የውድድር ዓመታት ብቅ ለማለት ሂውማን ብሪጅ ኢትዮጵያ ከተባለ ተቋም ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነትን ፈፅሟል፡፡

ክለቡ በፋሲል ቤተ መንግስት ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰብ ፕሮግራም ላይ የሂውማን ብሪጅ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አዳሙ አንለይ (ዶ/ር)፣ የክለቡ ፕሬዝዳንት እና የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ እንዲሁን ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዮት ብርሀኑ እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት የፊርማ ስነ ስርአቱ መደረጉ ሲገለፅ ስምምነቱ ለምን ያህል አመት የሚቆይ እንደሆነ አልተብራራም። በክለቡ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ በወጣው መረጃም ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የታኬታ፣ የኳስ፣ የመለያዎች እና የማሰልጠኛ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።