ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቀጣዩ ሳምንት ወደ እስራኤል ያመራል

በአሰልጣኝ እንድሪያስ ብርሀኑ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለወዳጅነት ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ቴላቪቭ ያቀናል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደ ችግር የሚነሳበትን በታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ያለመሥራት ድክመቱን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለማረም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ፣ ከስፔን እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ካሉ መሰል ተቋማት ጋር ግንኙነት እየፈጠረ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ አሁን ደግሞ ከእስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በቀጣዮቹ ዓመታት ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ለመሥራት ያሰበችውን ዕቅድ አንድ እርምጃ ፈቀቅ ለማድረግ ያለመ ግንኙነት መጀመሩን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ እንደ ቴክኒክ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሆነ ከሰሞኑ 48 ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች እና ክልሎች የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንድሪያስ ብርሀኑ መልምለው ከያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ልምምድ በካፍ አካዳሚ ብሔራዊ ቡድኑ ሲዘጋጅ የነበረ ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት ዕሁድ ሰኔ 6 ለወዳጅነት ጨዋታ ወደ እስራኤል ቴላቪቭ የሚያመራ ይሆናል፡፡

በዛሬው ዕለት 20 ተጫዋቾች ለጉዞው የተመረጡ ሲሆን 6 የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ጨምሮ በድምሩ 26 የልዑካን ቡድን በቀጣዩ ሳምንት እንደሚጓዙ ሰምተናል፡፡ ወደ ስፍራው ከሚጓዙ ተጫዋቾች መካከል ከዚህ በፊት ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የነበሩ ተጫዋቾች የተካተቱ ሲሆን 11 ተጫዋቾች ግን ከተለያዩ ክልሎች በአዲስ መልክ ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅለዋል፡፡ ይህ የወዳጅነት ጨዋታ አላማው እስራኤል ላለባት የአውሮፓ ሀገራት ማጣሪያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣዮቹ ዓመታት ለመሥራት ላሰበችው የታዳጊዎች ስልጠና፣ የስኮላርሺፕ ግንኙነት፣ የእግርኳስ ሜዲሲን ግንባታን በዋናነት ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የወዳጅነት ጨዋታው በፈረንጆች አቆጣጠር ጁን 15 እና 17 በቴላቪቭ የሚያደርግ ሲሆን ብሔራዊ ቡድናችንም በቀጣዩ ሳምንት ዕሁድ ወደ ቦታው የሚያመራም ይሆናል፡፡