ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ20ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃት አሳይተዋል ያልናቸውን ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ በማካተት ተከታዩን ምርጥ ቡድን መርጠናል።

አሰላለፍ 3-3-3

ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከቅርብ ተፎካካሪው ሲዳማ ቡና ጋር ያደረገውን ጨዋታ በድል እንዲወጣ የግብ ጠባቂው ሚና ከፍተኛ ነበር። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ያዳናቸው ለጎል የቀረቡ ጠንካራ ሙከራዎች ቡድኑ በፍፁም ቅጣት ምት ያገኛትን ግብ አስጠብቆ እንዲወጣ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበራቸው።

ተከላካዮች

ዳንኤል ደርቤ – ሀዋሳ ከተማ

በዚህም ሳምንት በተለመደው የታታሪነት ደረጃው ላይ የነበረው አንጋፋው የመስመር ተከላካይ የቡድኑን የቀኝ መስመር ጥቃቶች በማስጀመር በኮሪደሩ በኩል ማጥቃቱን ሲያግዝ ነበር። የቡድኑን ብቸኛ ጎል ወንድምአገኝ ሲያስቆጥርም ዳንኤል ኳስ በማቋረጥ እና ማጥቃቱን በማስጀመር ጉልህ ሚና ተወጥቷል።

ፍሬዘር ካሣ – ድሬዳዋ ከተማ

የውድድር ዓመቱን በአመዛኙ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የጀመረው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካይ በአሰልጣኝ ዘማሪያም ስር ዕምነት ተጥሎበት ተከታታይ ጨዋታዎችን እየተሰለፈ ይገኛል። በዚህ ሳምንትም ከበረከት ሳሙኤል ጋር ጥሩ መናበብን በመፍጠር የሲዳማን አጥቂዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እና በቡድን መከላከል ውስጥ ንቁ ሆኖ ተቆጣጥሯቸው አምሽቷል።

አሌክስ አሙዙ – ጅማ አባ ጅፋር

ተከላካይ ዳግም ወደ ሊጉ ከመጣ በኋላ በጅማ አባ ጅፋር ማልያ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ደካማ አቋም ሲያሳይ አልተመለከትነውም። ይበልጡንም በዚህ ሳምንት ጅማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የአየር ላይ ኳሶችን አደጋ በመከላከል እና የተጋጣሚን አጥቂዎች ተፅዕኖ በመቀነስ ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል።

ሄኖክ አርፊጮ – ሀዲያ ሆሳዕና

ለሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ ፀጋሰው ድማሙ ላስቆጠረው ኳስ የተሳካ ኳስ ያመቻቸው ሄኖክ ረጃጅም ኳሶች ለሚጠቀመው ቡድን የማጥቃት አማራጭ በመሆኑ ቀጥሎበታል። ተጫዋቹ ቡድኑን ነጥብ ካጋራው ጎል በተጨማሪም ሦስት የሚደርሱ አደገኛ ተሻጋሪ ኳሶችን ከግራ መስመር በኩል ማድረስ ችሎ ነበር።

አማካዮች

አማኑኤል ጎበና – ሀዲያ ሆሳዕና

አይደክሜው የመሐል አማካይ ፈታኝ የሆነው የፋሲል ከነማ የአማካይ ክፍል ጨዋታውን በሚፈልግበት መንገድ እንዳያስኬድ ሲታገል አምሽቷል። እንደ በዛብህ መለዮ ያሉ የተጋጣሚውን ፈጣሪ ተጫዋቾች በመቆጣጠርም ፋሲል ለማጥቃት ረጅም ኳሶችን እንዲጥል ሲያስገድድ ታይቷል።



ወንድምአገኝ ኃይሉ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳዎች የባህር ዳር ከተማ ተጫዋቾች ኳስ በነፃነት እንዳይዙ እና ቅብብሎችን እንዳይከውኑ ባደረጉት ጥረት ውስጥ ወጣቱ አማካይ በታታሪነት የሚጠበቅበትን አድርጓል። ከዚህም በላይ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ወሳኝ የነበረችውን ግብ የግል ክህሎቱን በሚያሳይ መልኩ ማስቆጠር ችሏል።

ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከሲዳማ ባደረገው ጨዋታ ላይ የሲዳማን የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴ ለመቋቋም እና ማጥቃቱን ለማገዝ የሱራፌል አስተዋፅዖ ወሳኝ ነበር። ተጫዋቹ የጥሩ አማካይነት ክህሎቱን ያሳየባቸው የጨዋታ ቅፅበቶች የነበሩ ሲሆን ከቅጣት ምት መነሻነትም አንድ ኢላማውን የጠበቀ ከባድ ሙከራ ማድረግ ችሏል። የጨዋታው መነሻ የነበረችው ፍፁም ቅጣት ምት የተገኘችውም በሱራፌል የማጥቃት ጥረት ነበር።

አጥቂዎች

ቸርነት ጉግሳ – ወላይታ ድቻ

ድሬዳዋ ላይ ማስገረሙን የቀጠለው ቸርነት ጉግሳ ለሦስተኛ ተከታታይ ሳምንት የምርጥ ቡድናችንን ተቀላቋል። ወጣቱ የመስመር አጥቂ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን እየሰበረ የሚገባበት መንገድ አሁንም ለድቻ ጥንካሬ እያላበሰው ነው። በዚህ ሳምንት ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ነጥብ ሲጋራም አንድ ግብ በማስቆጠር በሌላኛው ግብ ላይ ደግሞ ተሳትፎ አድርጓል።

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ጅማ አባ ጅፋር

አዲሱ የጅማ አባ ጅፋር ፈራሚ ልዩ በሆነ ብቃት ነው ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው። በመውረድ ስጋት ላይ ቢሆንም በከፍተኛ ትጋት ጨዋታውን ሲያከናውን በሚታየው ጅማ አባ ጅፍር የማጥቃት ሂደት ላይም የቀኙን መስመር ድርሻ ከፍ እንዲል አድርጓል። ለተመስገን ደረሰ ጎል ከዚሁ መስመር ግሩም ኳስ ያደረሰው ፕሪንስ በተደጋጋሚ የጊዮርጊስን የቀኝ የመከላክል መስመርን ሲያስጨንቅ ነበር።

ስንታየሁ መንግሥቱ – ወላይታ ድቻ

ቁመተ መለሎው አጥቂ በአስደናቂ የግንባር ኳስ እጅግ አስፈላጊ የነበረችውን የዓመቱ ሰናተኛ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል። ለቡድኑ የፊት መስመር ግርማ ሞገስ እየሆነ የመጣው ስንታየሁ በጎሉ ቡድኑን ወደ ጨዋታው ከመመለሱ ባለፈ በቸርነት ጎል ላይ የነበረውም ተሳትፎ በቦታው የሳምንቱ ተመራጭ አድርጎታል።

አሰልጣኝ – ሙሉጌታ ምኅረት (ሀዋሳ ከተማ)

በዚህ የውድድር ዓመት ሀዋሳ ከተማ ባገኛቸው ድሎች ላይ የአሰልጣኙ የጨዋታ አቀራረብ ትሎቁን ድርሻ ይወስዳሉ። በዚህ ሳምንትም ሀዋሳ ለረጅም ሳምንታት ያለሽንፈት የተጓዘው ባህር ዳርን 1-0 ሲረታ ለተጋጣሚው ፊት ያልሰጠ አቀራረቡ ውጤት አስገኝቶለታል። ባህር ዳሮች እንደልብ እንዳይቀባበሉ ከማድረግ አልፎ ወደ ግብ ክልላቸው እንዳይዘልቁ በማድረግ ረገድ የተሳካ ጊዜ ሲያሳልፉ የረባ ሙከራ ሳይደረግባቸው መውጣታቸውም የአሰልጣኙን አስተዋፅኦ የሚያጎላ ነው።

ተጠባባቂዎች

መሐመድ ሙንታሪ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ፀጋሰው ድማሙ (ሀዲያ ሆሳዕና)
በረከት ሳሙኤል (ድሬዳዋ ከተማ)
ረመዳን የሱፍ (ወልቂጤ ከተማ)
አለልኝ አዘነ (ሀዋሳ ከተማ)
ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)
ኦሴ ማውሊ (ሰበታ ከተማ)