ዛሬ ረፋድ ባህር ዳር ከተማ እና ዳሽን ቢራ የአምስት ዓመት የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ከአራት ሰዓት ጀምሮ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው ሥነ-ስርዓት ላይ የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፣ የዳሽን ቢራ የንግድ ክፍል ዳይሬክተር ሚስተር ፓትሪክ፣ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም አሰፋ እና የዳሽን ቢራ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አብርሃም ዘሪሁን ተገኝተዋል። ሁለቱ አካላት በይፋ ከመፈራረማቸው በፊትም ስለ ስምምነቱ መግለጫ ተሰጥቷል። በቅድሚያም የዳሽን ቢራ የንግድ ክፍል ዳይሬክተር ሚስተር ፓትሪክ ንግግር አድርገዋል።
“ከባህር ዳር ጋር አብረን መስራታችን ትልቅ ነገር ነው። እኛ እንደ ተቋም የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማሳደግ እንፈልጋለን። ዳሽን ቢራ የማኅበረሰቡ አንድ አካል ነው። ይህ ስለሆነም ተቋማችን ከማኅበረሰቡ ጋር ተባብሮ አብሮ መዝለቅ ይፈልጋል። የዛሬው ስምምነት በባህር ዳር ያለውን የእግርኳስ እድገት የሚያግዝ ነው። ስምምነቱ የረዥም ጊዜ ነው። ቀድሜ እንዳልኩት ግን የሀገሪቱም እግርኳስ ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ እናግዛለን። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም እስከ ዓለም ዋንጫ ድረስ እንዲደርስ እንመኛለን። በአጠቃላይ ዳሽን ቢራ ዛሬ በሚፈራረመው ስምምነት እጅግ ደስተኛ ነው።” ብለዋል።
ከፓትሪክ የመክፈቻ ንግግር በኋላ የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በአጭሩ ተከታዩን ብለዋል።
“ይሄ ስምምነት ባህር ዳር ከተማን ለመጠናከር የታሰበበት ስለሆነ ደስተኞች ነን። እኛ እንደ አመራር ክለቡን ለማጠናከር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራን ነው። የዛሬውም ስምምነትም የዚሁ አንድ አካል ነው። እንደምታቁት ፋሲል ከነማ የዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሆኗል። ለዚህ ድል ደግሞ ዳሽን ቢራ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። አሁን ደግሞ ባህር ዳርም አሸናፊ እንዲሆን ሊደግፈው መጥቷል። ለዚህም ደግሞ ዳሽን ቢራን በባህር ዳር ህዝብ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ።”
የተቀዳሚ ምክትል ከንቲባውን ንግግር ተከትሎም የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ አብርሀም አሰፋ ክለቡን በመወከል ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥተዋል።
“የዛሬው ቀን ለባህር ዳር ከተማ ትልቅ ቀን ነው። ክለቡ ዘንድሮ 40ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው። ይሄንን ዓመት በተደራጀ መልኩም ባይሆን እያከበርነው ነው። ባህር ዳር ከተማ በቀጣይ ዓመት አራት ቡድኖቹን (የወንዶች፣ የሴቶች፣ የመረብ ኳስ እና የእጅ ኳስ) በፕሪምየር ሊግ ውድድሮች ያሳትፋል። ዳሽን ቢራም የወንዶቹን ብቻ ሳይሆን አራቱንም ቡድኖች ነው የሚደግፈው። እርግጥ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ትዕዛዝ የህፃናት ቡድኖችንም ይዘናል። ግን በህጉ መሰረት የቢራ ምርት እነሱን ስለማይመለከት እነሱ ላይ ምርቱ አይተዋወቅም።
“ዋናውን የወንዶቹን ቡድን በተመለከተ በቀጣይ ዓመት የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ህልም ይዘን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ከዚህ ጎን ለጎን ክለቡ ራሱን እንዲችልም ስራዎች እየተሰሩ ነው። አሁን የመንግስት ክለብ ነው። በቀጣይ ግን ክለቡን የህዝብ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በቅርቡም የራሱ የተጫዋቾች ካምፕ እንዲኖረው ቦታ ተረክበናል። በተጨማሪም ገቢ ማመንጫ ህንፃም ለመገንባር እየለፋን ነው። በዚሁ ሁሉ ሂደት አጋራችን ዳሽን ቢራ አሁን ካለው ተወዳጅነት የበለጠ ተወዳጅ እንዲሆን ክለባችን የሚችለውን ያደርጋል። ተቋሙ ዛሬ ከምንፈራረመው ስምምነት በተጨማሪ በሰፋፊ ጉዳዮችም ሊያግዘን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ፍቃደኛ በመሆናቸው ደስታ ተሰምቶናል።”
መግለጫው ቀጥሎ የዳሽን ቢራ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ዘሪሁን ስለ ስምምነቱ ገለፃ ማድረግ ጀምረዋል። በገለፃቸውም ዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከተቋቋመ 20 ዓመት ማስቆጠሩን አውስተው ተቋማቸው በስፖርቱ ዘርፍ ያደረገውን ድጋፍ በማስከተል የስምምነቱን ጥቅል ጉዳይ አብራርተዋል።
“ዳሽን ቢራ 20 ዓመት ሞልቶታል። ተቋማችን ከተመሰረተ ጀምሮ በስፖርቱም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል። ባለፉት አምስት ዓመታት እንኳን ፋሲል ከነማን ለመደገፍ 105 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል። ቅድም እንደተባለውም ፋሲል ከነማ ዘንድሮ ሻምፒዮን ሆኗል። በዚሁ ጋር አያይዤም እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ሻምፒዮን እንዲሆንም የበኩላችንን አድርገናል። በዚህም ደግሞ ደስተኞች ነን። በዚህ የክለቡ ስኬት አሻራችንን በማሳረፋችንም ኩራት ይሰማናል።
“አሁንም ይሄንን ለመቀጠል ነው ከባህር ዳር ጋርም ስምምነት ለመፈፀም የመጣነው። ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም ከክለቡ ጋር በማሊያ ላይ አጋርነት አብረን እንዘልቃለን። በስምምነቱ መሠረትም 78 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል። ይሄ በውል የታሰረ ገንዘብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ክለቡ ገንዘብ ሊያገኝበት የሚችልበት መንገድ ካመቻቸ ልንረዳው ዝግጁ ነን። ከፋሲል ከነማ ጋርም የነበረው ነገር ይሄ ነው።” ብለው የስምምነቱ አንኳር ነጥብ አንስተዋል።
መግለጫውን ለመስጠት በቦታው የተገኙት አራቱ ግለሰቦች ንግግር ካሰሙ በኋላ የዳሽን ቢራ የህግ ክፍል አባል አቶ እንዳልካቸው አባይነህ እና የባህር ዳር ከተማ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እሱባለው ልይህ በተገኙበት ዳሽን ቢራ እና ባህር ዳር ከተማ ስምምነቱን በሚስተር ፓትሪክ እና አቶ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) አማካኝነት ፈፅመዋል።
ስምምነቱ ተፈፅሞ የማሊያ ትውውቅ ከተደረገ በኋላም በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ግልፅ መደረግ አለባቸው ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በተነሱት ጥያቄዎች መሰረትም የአጋርነት አከፋፈል መንገዱ ሁለቱን አካላት በሚመች መንገድ መሆኑን እና በየአመቱ መጠኑ እያደገ የሚመጣ መሆኑ፣ ዳሽን ቢራ ዋናው የወንዶቹን የእግርኳስ ቡድን ላይ በትኩረት መስራት መፈለጉ እና የዳሽን ቢራ ምርት ማሊያው ደረት ላይ እንደሚተዋወቅ በተሰጡት ምላሾች ተገልጿል።
በተያያዘ ዜናም ባህር ዳር ከተማ 2010 ላይ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ዘመናዊ አውቶብስ ለመግዛት ቃል ገብቶ የነበረው የክልሉ መንግስት ከሰሞኑን ቃሉን ጠብቆ ዘመናዊ አውቶብስ መግዛቱ ተነግሯል። የክልሉ መንግስት አውቶብሱን ለመግዛት የሰጠው ገንዘብ ላይም ወ/ሮ ትልቅሰው ገዳሙ ተጨማሪ ድጋፍ አድርገው አውቶብሱ መገዛቱ በመግለጫው መሃል ሲገለፅ ተሰምቷል።