የፈረሰኞቹ የግብ ዘብ የመኪና አደጋ ደርሶበታል

ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመቱን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያሳለፈው ግብ ጠባቂ ከቤተሰቦቹ ጋር መኪና እያሽከረከረ አደጋ እንደደረሰበት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

የውጪ ግብ ጠባቂዎችን በማስፈረም የሚታወቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከ2011 ጀምሮ ኬንያዊውን ፓትሪክ ማታሲን በማስፈረም ግባቸውን ሲያስጠብቁ ቆይተዋል። ሦስተኛ የውድድር ዓመቱን በኢትዮጵያ ዘንድሮ ያሳለፈው ማታሲ በ6ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በ10ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከወጣ በኋላ ወደ ሜዳ ሳይመለስ ቆይቶ የውድድር ዓመቱ ተገባዷል። ወደ ሀገሩ ኬንያ ከተመለሰ ቀናት ያስቆጠረው ግብ ጠባቂውም ከበድ ያለ የመኪና አደጋ ማስተናገዱ ተሰምቷል።

ባለቤቱን፣ ልጁን እና ሁለት ወንድሞቹን በቶዮታ ቪትስ መኪናው ጭኖ ከካካሜጋ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ የነበረው ተጫዋቹ መኪናው ቁጥጥር ውጪ ሆኖ መንገዱን በመሳቱ ምክንያት አደጋ መድረሱ ተሰምቷል። ዘ ስታንዳርድ እንደዘገበው ከሆነ በመኪናው ውስጥ የነበሩት ሁሉም ሰዎች ህይወት ሳያልፍ ከአደጋው መውጣታቸውን አትቷል። ተጫዋቹ በአሁኑ ሰዓትም በካፕሳቤት ሆስፒታል የህክምና ክትትል እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ተብሏል።

ፓትሪክ ማታሲ እና ቤተሰቦቹ በፍጥነት እንዲያገግሙ ሶከር ኢትዮጵያ ልባዊ ምኞቷን ትገልፃለች።

ያጋሩ