የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር ተቋቁሟል

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ደጋፊዎችን በአንድነት ለማሰባሰብ ዓላማ ያለው የደጋፊዎች ማኅበር ከሰሞኑን ተመስርቷል።

በሁሉም የሊግ እርከን፣ በሁለቱም ፆታዎች እና በሁሉም የእድሜ ክልል ያሉ ክለቦችን የሚደግፉ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ማዕቀፍ ለማድረግ ያለመው የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ መቋቋሙ ተገልጿል። 60 መስራች አባላትን ይዞ የተነሳው እና ህጋዊ ሰውነት ተሰጥቶት እንቅስቃሴ የጀመረው ማኅበሩ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለበት ሁሉ በመገኘት ድጋፍ ለመስጠት ማሰቡን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ምንያህል ጌታቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ፕሬዝዳንቱም ማኅበሩ በፕሪምየር ሊግ ላይ ያሉ የክለብ ደጋፊዎችን ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ክለቦችን የሚደግፉ የእግርኳስ ቤተሰቦችን ለማቀፍ ዓላማ እንዳለው ገልፀዋል።

በህጋዊነት ከተቋቋመ ገና አንድ ወር ያስቆጠረው ማኅበሩ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዳለው ተገልጿል። በተለይም ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማኅበሩ ቶሎ እንዲቋቋም ማበረታታቱን ገልፀው ፌዴሬሽኑ ቢሮ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውንም አውስተውናል። አቶ ምንያህል አያይዘውም ቋሚ ቢሮውን እስኪያገኙ ድረስ ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ በጊዜያዊነት በስታዲየም በሚገኝ ጊዜያዊ ቢሮ የአባላት ምዝገባ እንደሚጀምሩ አስረድተውናል። አባል ለመሆንም ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ መስፈርቱ እንደሆነ ነግረውናል።

አቶ ምንያህል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሚያደርግላቸው እገዛ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ በቀጣይ ዓመት የኮቪድ-19 ህግጋቶች ሳይጣሱ ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየም ለማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው እና ለሚመለከታቸው አካላትም ጥያቄ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ነግረውኗል።