ሁለቱ ወጣት ተጫዋቾች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ?

ለ2014 የውድድር ዘመን ስብስባቸውን ለማጠናከር ከወዲሁ መንቀሳቀስ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሁለት ወጣት ተጫዋቾች ጋር ቅድመ ስምምነት እንደሚያርጉ ይጠበቃል።

የእግርኳስ ህይወታቸውን በወላይታ ድቻ ከ17 ዓመት በታች ቡድን የጀመሩት በረከት ወልዴ እና ቸርነት ጉግሳ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ አድገው ባለፉት አራት የውድድር ዓመታት የተሳካ ጊዜ ማሳለፋቸው ይታወቃል። በተለይ በዘንድሮው ዓመት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለቱም ድንቅ አቋማቸውን ሲያስመለክቱን መሰንበታቸው ይታወሳል። ከወላይታ ድቻ ጋር ያላቸው ኮንትራት በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ መሆኑን ተከትሎ ሁለቱን ተጫዋቾችን ለማስፈረም የተለያዩ የሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ክለቦች ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ሲነገር የቆየ ቢሆንም በስተመጨረሻ በቀጣይ ዓመት ማረፊያቸው እንዲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊሆን ተቃርቧል።

ተጫዋቾቹ ከትውልድ ከተማቸው ወላይታ ሶዶ በመምጣት በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆን የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር በዛሬው ዕለት ቅድመ ስምምነት ፊርማቸውን ያኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለምን ያህል ጊዜ ኮንትራት እንደሚፈርሙም ረፋድ ከሚኖራቸው ድርድር በኋላ የሚታወቅ ይሆናል። ተጫዋቾቹ ቅድመ ስምምነት ይፈፅሙ እንጂ የ2014 የውድድር ዘመን የዝውውር መስኮት በቀጣይ ወራት ሲከፈት የተጫዋቾቹ ውል የሚፀድቅ ይሆናል።

ፈረሰኞቹ በቅርቡ ሌሎች ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ቅድመ ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።