የመኪና አደጋ ያስተናገደው ፓትሪክ ማታሲ ስለ ጤንነቱ ተናግሯል

ከትናንት በስትያ የመኪና አደጋ ያጋጠመው ኬንያዊው የግብ ዘብ ስለ ወቅታዊ ጤንነቱ ሀሳብ ሰጥቷል።

ከ2011 ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሲጫወት የነበረው ኬንያዊው ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ከትናንት በስትያ በቶዮታ ቪትስ መኪናው ባለቤቱን፣ ልጁን እና ሁለት ወንድሞቹን ጭኖ ከካካሜጋ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ አደጋ አስተናግዶ ነበር። የሀገሪቱ የብዙሃን መገናኛዎችም ከአደጋው በኋላ የተለያዩ መረጃዎችን ሲያወጡ የነበረ ቢሆንም ከደቂቃዎች በፊት ራሱ ፓትሪክ ማታሲ በግል የቲዊተር ገፁ ስለ ጤንነቱ ተከታዩን መልዕክት አስተላልፏል።

“እንዴት አደራችሁ ጓደኞቼ። ቤተሰቤ እና እኔ የመኪና አደጋ ከደረሰብን ጀምሮ ስትጨነቁልን ነበር። አሁን በጣም ደህና እንደሆንኩ እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ከምንም በላይ ፈጣሪ በህይወት ስላተረፈን አመሠግናለሁ።

“አሁን ደህና ነኝ። ባለቤቴ በመጪው ሰኞ የቀዶ ጥገና ታከናውናለች። ልጄ ገና አልተረጋጋም። ግን በሀኪሞች ክትትል ስር ነው።” የሚል መልዕክቱን አስተላልፎ ስለ እርሱ እና ቤተሰቡ የተጨነቁትን ወዳጆቹን አመስግኗል።