ቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና ዕውነታዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጰያ ፕሪምየር 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዙርያ ያጠናቀርነውን ቁጥራዊ መረጃ እና ዕውነታ እንደሚከተለው አሰናድተናል።

የጎል መረጃዎች

– በዚህ ሳምንት በተደረጉት ስድስት ጨዋታዎች 12 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህ ካለፈው ሳምንት በአራት ዝቅ ያለ የጎል ቁጥር ሆኗል።

– ከአስራ ስድስቱ ጎሎች መካከል ስምንት ጎሎች የተቆጠሩት ከዕረፍት በፊት ሲሆን አራት ጎሎች ብቻ ከዕረፍት በኋላ ተቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩ ጎሎች መካከል አንድ ብቻ በፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥሯል። የድሬዳዋ ከተማው ሙኅዲን ሙሣ ብቸኛው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አስቆጣሪ ነው።

– እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ በዚህ ሳምንትም ከቆሙ ኳሶች መነሻነት የሚቆጠሩ ጎሎች በርከት ብለዋል። ሙኅዲን ሙሣ ከፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር ጌታነህ ከበደ እና በዛብህ መለዮ ከማዕዘን ምት በግንባር በመግጨት፣ ፀጋሰው ድማሙ ከቅጣት ምት በግንባር በመግጨት እንዲሁም በላይ ዓባይነህ በቀጥታ ቅጣት ምት አስቆጥረዋል። ረመዳን የሱፍ እና ዓለማየሁ ሙለታም በቀጥታ ባይሆንም ያስቆጠሯቸው ጎሎች መነሻቸው የቆመ ኳስ ነበር።

– በዚህ ሳምንት አስር ኳሶች ሳጥን ውስጥ ተመትተው ወደ ጎልነት ሲቀየሩ ሁለት ብቻ ከሳጥን ውጪ ተመትተው ተቆጥረዋል።

– 12 ተጫዋቾች በጎል አስቆጣሪነት ስማቸውን አስመዝግበዋል። ሁሉም ተጫዋቾች አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

– ከሳምንቱ አስቆጣሪዎች መካከል በላይ ዓባይነህ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ጎሉን አስቆጥሯል።

የሳምንቱ ስታቶች
(ቁጥሮቹ የተገኙት ከሱፐር ስፖርት ነው)

ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ

ከፍተኛ – ሰበታ ከተማ (7)
ዝቅተኛ – ባህር ዳር ከተማ (1)

ጥፋቶች

ከፍተኛ – ሀዲያ ሆሳዕና (24)
ዝቅተኛ – ጅማ አባ ጅፋር (12)

ከጨዋታ ውጪ

ከፍተኛ – ባህር ዳር ከተማ (7)
ዝቅተኛ – ድሬዳዋ፣ ሀዋሳ፣ ሆሳዕና (1)

የማዕዘን ምት

ከፍተኛ – ፋሲል ከነማ (12)
ዝቅተኛ – ድሬዳዋ ከተማ (1)

የኳስ ቁጥጥር ድርሻ

ከፍተኛ – ሲዳማ ቡና (59%)
ዝቅተኛ – ድሬዳዋ ከተማ (41%)

የዲሲፕሊን ቁጥሮች

– በዚህ ሳምንት 25 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዘዙ አንድ ቀይ ካርድ ተመዟል።

– የዚህ ሳምንት ቁጥር ካለፈው ሳምንት በ1 የቢጫ ካርድ የበለጠ ነው።

– የሰበታ ከተማው ዳዊት እስጢፋኖስ (ሁለት ቢጫ) በዚህ ሳምንት ብቸኛው የቀይ ካርድ ሰለባ የሆነ ተጫዋች ሆኗል። ተጫዋቹ በቢጫ ካርድ ጨዋታውን ቢጨርስም ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል።

– ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ እያንዳንዳቸው 4 ቢጫ ካርድ በማስተናገድ ቀዳሚዎች ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ (1) ዝቅተኛውን ቁጥር አስመዝግቧል።

– ምኞት ደበበ እና ባዬ ገዛኸኝ የውድድር ዓመቱን አምስተኛ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክተው ቀጣይ ጨዋታ የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው።

በመጀመርያ ንክኪ ጎል

የአዳማ ከተማው አጥቂ በላይ ዓባይነህ በ90ኛው ደቂቃ የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ በማስቆጠር ክለቡ ከወልቂጤ ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሏል። ተጫዋቹ ይህን ጎል ያስቆጠረው በመጀመርያ የኳስ ንክኪው ሲሆን ከሳለአምላክ ተገኘ እና ቃልኪዳን ዘላለም በመቀጠል በውድድር ዓመቱ ይህን ያሳካ ሦስተኛው ተጫዋች ሆኗል።

የባህር ዳር እና ሀዋሳ ጨዋታ አስገራሚ ግጥጥሞሽ

ባህር ዳር ከተማ በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሸነፉን ተከትሎ ከ11 ጨዋታ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ ሽንፈት ያስተናገደው በ7ኛው ሳምንት ጅማ ላይ በሀዋሳ 2-1 ሲሆን ከአስራ አንድ ጨዋታ በኋላም ይህ መልካም ጉዞው በሀዋሳ ከተማ መገታቱ ግጥጥሞሹን አስገራሚ ያደርገዋል።

ጎሎች የበረከቱባቸው ደቂቃዎች

በፕሪምየር ሊጉ በርካታ ጎሎች ከሚቆጠርባቸው ደቂቃዎች መካከል ተጫዋቾች ትኩረት የሚያጡባቸው የየአጋማሾቹ የመጀመርያ ደቂቃዎች እና ድካም የሚኖርባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች እንደሆኑ በበርካታ አጋጣሚዎች ታይቷል። በዚሀ ሳምንትም ወደ እረፍት መዳረሻ እና ከእረፍት በኋላ ባሉ የመጀመርያ ደቂቃዎች በርካታ ጎሎችን ተመልክተናል።

በዚህ ሳምንት ከተመዘገቡ 12 ጎሎች መካከል ስንታየሁ መንግሥቱ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ሙኅዲን ሙሳ እና ረመዳን የሱፍ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ጎል ሲያስቆጥሩ በዛብህ መለዮ እና ተመስገን ደረሰ ደግሞ ከእረፍት በኋላ ባሉ የመጀመርያ ደቂቃዎች አስቆጥረዋል።

በሁለት ጎል ልዩነት ከመመራት ወደ አቻ

ወላይታ ድቻ ከሰበታ ከተማ ባደረገው ጨዋታ 2-0 ከመመራት ተነስቶ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት መለያየት ችሏል። ይህም በውድድር ዓመቱ ወልቂጤ ከተማ (ከኢትዮጵያ ቡና 2-2) በአንደኛ ሳምንት ካሳካ ወዲህ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።

© ሶከር ኢትዮጵያ