“ራሱን ያጠፋው ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ አይደለም” – የሰዒድ አባት ዋልተር ቪሲን

ከትናንት በስትያ ራሱን አጥፍቶ የተገኘው የሰዒድ ቪሲን አባት (የማደጎ አባት) ልጃቸው “በዘረኝነት ችግር ራሱን አጥፍቷል” የተባለውን መረጃ አስተባብለዋል።

በኢትዮጵያ የተወለደው ሰዒድ በጣልያናዊው የቪሲን ቤተሰብ በ7 ዓመቱ በማደጎነት ወደ አውሮፓ ማምራቱ ይታወቃል። የእግርኳስ ፍቅር የነበረው ታዳጊውም በቅድሚያም በኤሲ ሚላን አካዳሚ ከዛም ወደ ቤንቬንቶ አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን ጀምሮ ነበር። 2016 ላይ ግን እግርኳስ በቃኝ ብሎ ወደ ሌላ ሙያ የገባ ሲሆን ከትናንት በስትያም በመኖሪያ ቤቱ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል። የወጣቱ ህልፈት ከተሰማ በኋላም ኮሪዬሬ ዴላ ሴራ የተባለው ጋዜጣ ወጣቱ “ከመሞቱ በፊት ፅፎ ያስቀመጠውን መልዕክት አግኝቻለው” ብሎ ይፋ አድርጎ ነበር። ጋዜጣው ሰዒድ ቪሲን በዘረኝነት ችግር ተማሮ ራሱን ለማጥፋት መበረታታቱን ቢዘግብም በማደጎነት ወደ ጣሊያን የወሰዱት አባቱ ግን በጋዜጣው የወጣው መልዕክት ከበርካታ ዓመታት በፊት የፃፈው መሆኑን ተናግረዋል። አባትየውም “ቪሲን ራሱን ያጠፋው የመገለል ስሜት ስለተሰማው አይደለም።” ብለዋል።

“ልጄ ከመሞቱ በፊት ፃፈው የተባለው መልዕክት የቆየ ነው። 2019 ላይ የተፃፈ ነው። ራሱንም ያጠፋው የመገለል ስሜት ስለተሰማው አይደለም። እናም ሁላችሁም ይሄንን ውሸት እንዳታምኑ እጠይቃለሁ። አንዳንድ ጊዜ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎች አሉ። እንደ ማንኛውም ወጣትም ደስተኛ አለመሆኑን ሊገልፅ ይሆናል።

“እዚህ (ጣሊያን) ሁሉም ሰው ልጄን ይወደዋል። እርሱም እንደዛው። ዛሬ ከቀጥር በፊት ሥርዓተ-ቀብሩ በቤተክርስቲያን በርካታ ቤተሰቦቹ እና ወጣቶች ባሉበት ይከናወናል። ፅፎታል የተባው መልዕክት በወቅቱ በጣሊያን በነበረው ነገር በብስጭት የተፃፈ ነው። ግን ራሱን ከማጥፋቱ ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም።” የሚል ሀሳባቸውን ልጁን ገና በ7 ዓመቱ በማደጎነት ወደ ጣሊያን የወሰዱት ዋልተር ቪሲን ለሪፐብሊካ ጋዜጣ ተናግረዋል።