የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሾሟል

የመዲናው እግርኳስ ፌዴሬሽን አቶ ኃይለየሱስ ፍሰሐን (ኢ/ር) ከፕሬዝዳንትነት በማገድ አዲስ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት መሾሙ ተሰምቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቱ የነበሩትን ኃይለየሱስ ፍሰሃ (ኢ/ር) “በአምስት ተከታታይ መደበኛ ስብሰባዎች ላይ አለመገኘታቸውን ተከትሎ” ከስልጣናቸው ማገዱ ተሰምቷል። ፕሬዝዳንት የማውረድም ሆነ የመሾመም ስልጣን ያለው ጠቅላላ ጉባዔው ቢሆንም ፌዴሬሽኑ “ጠቅላላ ጉባዔው እስኪጠራ ድረስ ሥራ እንዳይበደል እና ፕሬዝዳንቱ በሥራ ገበታቸው ላይ በተደጋጋሚ ባለመገኘታቸው” በሚል በሥራ አስፈፃሚዎቹ አማካኝነት ባደረገው ስብሰባ ጊዜያዊ የፕሬዝዳንት ለውጥ አከናውኗል።

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሠረት ፕሬዝዳንት የነበሩት ኃይለየሱስ ፍሰሃ እንዲነሱ ተደርገው የሥራ አስፈፃሚ ሽግሽግ ተደርጓል። በዚህም የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ ጠቅላላ ጉባዔው እስኪደርስ ድረስ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ ተወስኗል። እርሳቸው በነበሩበት የምክትል ፕሬዝዳንት ሚና ደግሞ የማርኬቲንግ ክፍል ኃላፊ የነበረው አቶ ደረጄ አረጋ እንዲሠራ ሆኗል።