የትግራይ ክልል ክለቦች በቀጣይ ዓመት በሊጉ የማይሳተፉ ከሆነ እነርሱን ለመተካት ውድድር የሚያደርጉት ስድስቱ ክለቦች አሁን ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ሶከር ኢትዮጵያ አጣርቷል።
በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በፀጥታ ጉዳዮች ምክንያት ያልተሳተፉት ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች መቐለ 70 እንድርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ በቀጣይ ዓመትም ወደ ውድድሩ የመመለሳቸው ጉዳይ እስካሁን አለየለትም። ምንም እንኳን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር መቀመጫቸውን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ካደረጉት ክለብ አመራሮች ጋር ንግግር ቢጀምሩም የቀጣይ ዓመት ተሳትፏቸው ጉዳይ የቆረጠለት ውሳኔ አላገኘም። የሊጉ አስተዳዳሪ አክሲዮን ማኅበሩም ክለቦቹ ከሐምሌ 1-15 ድረስ ምዝገባ የሚያከናውኑ ከሆነ በቀጣይ የውድድር ዓመት እንደሚሳተፉ ያለበለዚያ ግን ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት እንደሚገደድ ማስታወቁ ይታወሳል።
የሀገሪቱ እግርኳስ የበላይ የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ የትግራይ ክልል ክለቦቹ እስከተባለው ጊዜ (ሐምሌ 15) ድረስ መሳተፋቸውን ካላረጋገጡ ሁለተኛ አማራጭ አስቀምጧል። ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስትያ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረትም ክለቦቹን ተክቶ በቀጣይ ዓመት የሚደረገው የሊግ ውድድር በ16 ክለቦች መካከል እንዲደረግ ዘንድሮ ከሊጉ የወረዱት አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ወልቂጤ ከተማ ከሦስቱ የከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ካጠናቀቁት ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር የአንድ ዙር የነጥብ ጨዋታ አድርገው የተሻለ ነጥብ ያገኙት ክለቦች የማይሳተፉትን የትግራይ ክልል ክለቦች ቦታ እንደሚይዙ አስረድቷል። ይሄንን ውሳኔ ተከትሎም የትግራይ ክልል ክለቦችን ጉዳይ በጎን እየተመለከቱ በቀጣይ ዓመት ለሚደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመሳተፍ የመጨረሻ ዕድላቸውን ለመሞከር አጋጣሚ ያገኙት ስድስቱ ክለቦች ሰኔ 18 በሀዋሳ ከተማ ለሚደረገው የእርስ በእርስ ግጥሚያ ዝግጅታቸው ምን እንደሚመስል አጣርተን ተከታዮቹን መረጃዎች አግኝተናል።
በዘንድሮው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዡን ግርጌ ይዞ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ በአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ አምስቱን ወሳኝ ጨዋታዎች ለማድረግ ከፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 5 ጀምሮ ዝግጅት እንደሚጀምር ሰምተናል። ክለቡ በአሁኑ ሰዓት በእረፍት ላይ የሚገኙትን ተጫዋቾችንም ቅዳሜ ውድድሩ በሚደረግበት ሀዋሳ ከተማ እንዲገኙ ጥሪ ማቅረቡ ታውቋል። ተጫዋቾቹ ቅዳሜ ሀዋሳ ከተገኙ በኋላም ከእሁድ ጀምሮ ልምምድ መስራት እንደሚጀምር ተነግሯል።
ከአዳማ ከተማ በአንድ ነጥብ ልቆ 12ኛ ደረጃን በመያዝ የውድድር ዓመቱን ያገባደደው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ከበርካታ የሜዳ ውጪ ጥያቄዎቹ ጋር በመሆን በሊጉ ለመቆየት ያገኘውን የመጨረሻ ዕድል ለመጠቀም እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከትናንት በስትያ ከወላይታ ድቻ ጋር ቅድመ ስምምነት በፈፀሙት ዋና አሠልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው ቡድኑም በአሁኑ ሰዓት ከደሞዝ ጋር በተገናኘ ተጫዋቾቹን ልምምድ ለማሰራት እንደተቸገረ አውቀናል። የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ተጫዋቾችን ደሞዝ ለወራት ያልከፈለው ክለቡ ተጫዋቾቹ በቶሎ የደሞዝ ጥያቄያቸውን መልሶ ወደ ዝግጅት ለመግባት ነገ ቀጠሮ እንደያዘ ሰምተናል። አመራሮቹም ከተሳካ ነገ አልያም ከነገ በስትያ ለተጫዋቾቹ ደሞዝ ከፍለው ከአሠልጣኛቸው ፀጋዬ ጋር ዝግጅት እንዲጀምሩ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምም ዛሬ ጅማ ከተማ እንደገቡ ያረጋገጥን ሲሆን አሠልጣኙም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ 1:30 ድረስ ከክለቡ አመራሮች ጋር ስብሰባ እንዳደረጉ የደረሰን መረጃ ያመላክታል። በውይይቱም ችግር ተብለው የተቀመጡ ተግዳሮቶች ቶሎ እንዲፈቱ መፍትሄ ተቀምጧል። በአጠቃላይ ጅማ አባጅፋር ለተጫዋቾች የሚገባው ደሞዝ ነገ አልያም ከነገ በስትያ ከፍሎ እንደጨረሰ ተጫዋቾቹን እስከ ቅዳሜ ሰብስቦ የፊታችን እሁድ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት ቋሚ ልምምዱን ሀዋሳ ላይ እንደሚጀምር ተረድተናል።
እንደ ጅማ እና አዳማ በሁለት አሠልጣኞች የውድድር ዓመቱን የቋጨው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከዝግጅት በፊት መሰራት ያለባቸውን ሥራዎች እየከወነ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል። ክለቡ በግልፅ ያላሳወቀንን ሥራዎች በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ካገባደደ በኋላም በቀጥታ ለተጫዋቾች ጥሪ አቅርቦ ዝግጅቱን እንደሚጀምር አውቀናል።
በከፍተኛ ሊግ ሦስቱ ምድቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት ክለቦችንም ዝግጅት አጣርተናል። በምድብ ሀ ውድድሩን ሲያደርግ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ታሪክ ወደፃፈበት የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ እርከን ለመመለስ ዝግጅቱን ጀምሯል። በዚህም በአሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የሚመራው ቡድኑ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል መቀመጫውን በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ ልምምድ እየሠራ እንደሚገኝ ሲታወቅ ወድድሩ ሊጀመር አምስት ቀናት ሲቀሩትም ወደ ሀዋሳ ለማምራት ሀሳብ እንዳለው ተነግሯል።
በምድብ ለ 44 ነጥቦችን በመያዝ አንደኛ ሆኖ በቀጥታ ወደ ሊጉ ያለፈው አዲስ አበባ ከተማን በመከተል 2ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ያገባደደው ሀምበሪቾ ዱራሜ በበኩሉ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተላለፈውን ውሳኔ በይፋዊ ደብዳቤ ካገኘ በኋላ ወዲያው ወደ ሥራ ገብቷል። ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሠረትም ተጫዋቾች በአሠልጣኝ ግርማ ታደሰ መሪነት ከነገ ጀምሮ እንዲሰባሰቡ ጥሪ እንደቀረበ ተመላክቷል። በዱራሜ ከተማ ተጫዋቾቹ ከተሰባሰቡ በኋላ ወዲያው ልምምድ እንዲጀምሩ ተደርጎ የሀዋሳው ውድድር ሊጀምር አንድ ሳምንት ሲቀረው ወደ ስፍራው ለመጓዝ እቅድ እንደተያዘም ታውቋል።
በአሠልጣኝ መሐመድኑር ንማ የሚመራው እና ከያዘው ስብስበ እንዲሁም ካለው በጀት አንፃር እጅግ አስደናቂ ጉዞ አድርጎ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ደግሞ ከሌሎቹ ክለቦች በተለየ ቀድሞ ዝግጅት ላይ ከርሞ እንደነበር ተነግሮናል። “የሚመጣው ነገር አይታወቅም” በማለት የ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድር ካለቀ ከሳምንታት በኋላ ዝግጅት የጀመረው ክለቡ ለተወሰኑ ቀናት ልምምዱን ከሠራ በኋላ ተጫዋቾቹን ለእረፍት በትኖ ነበር። ከትናንት በስትያ የተወሰነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ ከተሰማ በኋላ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ የተሳተፈ በታሪክ የመጀመሪያው የክፍለ ከተማ ክለብ ለመሆን ያለመው ክለቡ ከትናንት ጀምሮ መደበኛ ዝግጅቱን እንደጀመረ አውቀናል።