የኢትዮጵያ እግርኳስ የወቅቱ መነጋገርያ ዕርስ በሆነው አቡበከር ናስር ዙርያ የክለቡን አቋም አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቡና ቦርድ ሰብሳቢ ለሶከር ኢትዮጵያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እጅግ የተሳካ ዓመት በማሳለፍ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች፣ የዓመቱ ምርጥ ታዳጊ ተጫዋች እና የዓመቱ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር ያገኘው አቡበከር ናስርን ካሳለፍነው ዓመት ጀምሮ የግላቸው ለማድረግ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ክለቦች ፍላጎት ሲያሳዩ ቆይተዋል። በተለይ ግን ዘንድሮ ከሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ጀምሮ የደቡብ እና ሰሜን አፍሪካ ክለቦች ጥያቄ ቢያቀርቡም አቡበከር ከነበረበት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ፉክክር አንፃር ሳይሳካ ቀርቷል። አሁን የውድድሩ መጠናቀቅ ተከትሎ እና አቡበከር ካሳካው ስኬት አንፃር ከላይ የተጠቀሱት የአፍሪካ ሀገራትን ጨምሮ የምስራቅ አውሮፓ እና የኤዥያ ሀገራት ተጫዋቹን ለማስፈረም ግልፅ በሆነ ደብዳቤ እና በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ለኢትዮጵያ ቡና ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነ ማረጋገጥ ችለናል። አቡበከር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያቆየው ቀሪ የአራት ዓመት ኮንትራት ያለው በመሆኑ በተጫዋቹ ዙርያ እየቀረቡ ላሉ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ያልሆኑ ጥያቄዎች ክለቡ ከምን አንፃር እየተመለከተ ነው ስንል የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞን አናግረን ይሄን ብለውናል።
” እኛ ሀገር ብዙ የተምታታ ነገር አለ። የተጫዋች ወኪሎች፣ ክለቦች እና ተጫዋቾቹ መብታቸውን እና ግዴታቸውን ጠንቅቀው አለማወቅ ነው። ሁሉም በራሱ መንገድ ስለሄደ እና በማኅበራዊ ሚድያ ይሄ ክለብ ሊሄድ ነው፤ ይሄ ሊወስደው ነው በማለት ስለፃፍክ በፍፁም የሚመጣ ነገር የለም። ሥርዓት አለው ማንኛውም ነገር፤ ክለቡ ጋር መድረስ አለበት። ክለቡም የራሱን መብት እንዲሁም የልጁን መብት ቁጭ ብሎ ይመለከታል። ከዚህ ውጭ የሚከሰቱ ነገሮች ህገወጥ ናቸው። አስፈላጊ ከሆነ ወደ ሊግ ካምፓኒው እንዲሁም ወደ ፌዴሬሽኑ በመሄድ ህጋዊ እርምጃ ማስወሰድ እንችላለን። ሆኖም የሚመጡ ህጋዊ ጥያቄዎች ካሉ አቡበከር ባለቤትነቱ የክለቡ ነው። የአራት ዓመት ቀሪ ኮንትራት አለው። አንዳንድ ክለቦች አንሸጥም ሊሉ ይችላሉ። እኛም አንሸጥም የማለት መብት አለን። ግን እኛ የአቡበከርን የተሻለ ደረጃ መድረስና ዕድገቱን እንፈልጋለን። ይህ ልጅ ወደ አውሮፓ ወይም ወደ ተሻለ ክለብ ሄዶ እንዲጫወት እንፈልጋለን። ዞሮ ዞሮ ለልጁም ዕድገት ለሀገርም ጥቅም እንዲሁም ለክለቡ ትልቅ ክብር እና ስም ነው። የሚመጡትን ጥያቄዎች ቁጭ ብለን በማየት ለእኛም ለእሱም ጠቃሚ የሆነ ውሳኔ እንወስናለን። ከዚህ ወጭ በአሉባልታ እና በወሬ የሚሆን ነገር እንደሌለ እንዲታወቅ እንፈልጋለን።”