በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በየጨዋታ ሳምንቱ ምርጥ 11 ተጫዋቾችን ያካተተ ቡድን ስንሰራ መሰንበታችን የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ የዓመቱን ምርጥ ቡድን እና ምርጦችን እንዲህ መርጠናል።
አሰላለፍ 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
በ2010 የውድድር ዓመት ፋሲል ከነማን የተቀላቀለው ማሊያዊው ግብ ጠባቂ በወጥነት ክለቡን በማገልገል ላይ ይገኛል። ዘንድሮ በ21 ጨዋታዎች የቡድኑ የግብ ዘብ በመሆን መሰለፍ የቻለው ግብ ጠባቂው በ11 ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ከሜዳ መውጣት ችሏል። 2012ን ሳይጨምር በቡድኑ ሦስተኛ የውድድር ዓመቱን ያሳለፈው ሳማኬ ከተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቹ ጋር ጥሩ መግባባትን ባሳየባቸው በዘንድሮዎቹ ጨዋታዎች ይታይበት የነበረው ከፍተኛ ትኩረት በተቻለው መጠን ራሱን ከስህተቶች ከመጠበቅ ባለፈ ከተጋጣሚዎች የሚሰነዘሩ አደገኛ ኳሶችን በማዳን ረገድ ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል። ተጫዋቹ በዓመቱ በአማካይ ያስተናግድ የነበረው የግብ መጠን 0.6 ብቻ መሆኑ ለስኬቱ ምስክር ነው።
ተከላካዮች
እንየው ካሣሁን – ፋሲል ከነማ
ለፌዴራል ፖሊስ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ ተጫውቶ ያሳለፈው የቀኝ መስመር ተከላካዩ የእግር ኳስ ህይወቱን ምርጡን የውድድር ዓመት አሳልፏል። የፋሲል የቦታው ዋና ተሰላፊ ለነበረው ሰዒድ ሀሰን ሁለተኛ ዕቅድ ይመስል የነበረው እንየው ሰዒድ 6ኛው ሳምንት ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር በተደረገ ጨዋታ ከባድ ጉዳት ባስተናገሰበት ቅፅበት ተቀይሮ ከገባ በኋላ በ 19 ጨዋታዎች በቀዳሚነት መሰለፍ ችሏል። ተጨዋቹ አጋጣሚው የፈጠረለትን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ከመከላከሉ ባለፈ የቡድኑ የቀኝ መስመር በማጥቃቱ ረገድ ላሳየው ጥንካሬ አንዱ መነሻ መሆን ችሏል። ከመስመር አጥቂዎች ጋር ጥሩ መናበብ በመፍጠር እስከተጋጣሚ የግብ ክልል ድረስ በመሄድ ወደ ግብ ከሚልካቸው አደገኛ ኳሶች መነሻነትም ለአራት ግቦች መቆጠር ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።
ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ
በተከላካይ አማካይነት ደደቢትን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ብቅ ያለው ኩሊባሊ አልፎ አልፎ በመሀል ተከላካይነት ላይ እየተመለከትነው የነበረ ሲሆን ወደ ፋሲል ከነማ ከመጣ በኋላ ግን ቦታው በልኩ የተሰፋ ስለመሆኑ ማሳያ የሆነ ብቃትን ማሳየት ችሏል። ከያሬድ ባየህ ጋር ድንቅ ጥምረት ያሳየው ኮትዲቯራዊው ተከላካይ ቡድኑ ዋንጫ ማንሳቱን እስኪያረጋግጥ ባልተዛነፈ ሁኔታ ሜዳ ላይ ተመልክተነው በድምሩ በ22 ጨዋታዎች ቀዳሚ ተሰላፊ መሆን ችሏል። በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ውስጥ አሸናፊ በመሆን የተጋጣሚን ቁልፍ አጥቂዎች እንቅስቃሴ በመገደብ ኩሊባሊ ለፋሲል የተከላካይ ክፍል ብርታት መሆን ችሏል። አስፈላጊ ሲሆን ወደ ፊት ወጣ እያለ አካላዊ ጥንካሬውን በመጠቀም ኳሶችን ያቋርጥ የነበረባቸው ቅፅበቶችም ለአፄዎቹ ስኬት ወሳኝ ሆነው አልፈዋል።
ያሬድ ባየህ – ፋሲል ከነማ
የአፄዎቹ አምበል ለቡድኑ እጅግ በጣም አስፈላጊው ተጫዋች ነው። ሜዳ ላይ ቡድን በሚመራበት መንገድ ተጫዋቾችን በማስተባበር እና ከፍ ባለ ፍላጎት ጨዋታቸውን እንዲያከናውኑ በማድረግ ያሬድ ጉልህ ሚና ሲወጣ ይታያል። ከኳስ ጋር እጅግ የተረጋጋ የሆነው ተከላካዩ በራሱ የግብ ክልል ውስጥ ተጋጣሚዎች በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው እንኳ ሳይረበሽ እንቅስቃሴዎችን ሲከውን ይታያል። መከላከልን ምርጫቸው ካደረጉ ቡድኖች ጋርም እስከ መሀል ሜዳ ድረስ በመሄድ የተሳኩ ቅብብሎችን እያደረገ የፋሲልን ጥቃት ሲያሳልጥ ዓመቱን አሳልፏል። በዓመቱ ከከድር ኩሊባሊ ጋር ከነበረው ጥምረት በተጨማሪ ከዳንኤል ዘመዴ ጋር በአንድ ጨዋታ አብሮ የተሰለፈበትን ጨምሮ 23 ጊዜ ቡድኑን ከኋላ የመራው ያሬድ ፋሲል የዋንጫ ጉዞውን ባሳመረበት በወሳኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ የዓመቱን ብቸኛውን ግን ደግሞ እጅግ አስፈላጊዋን ጎሉንም ማስቆጠር ችሏል።
አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና
በግራ መስመር ተከላካይ ምርጫችን ላይ ከአምሳሉ ጥላሁን እና ረመዳን የሱፍ ጋር የተፎካከረው አሥራት ቱንጆ በስምንት ግቦች ላይ በነበረው ቀጥተኛ ተሳታፊነት ምክንያት ተመራጭ ሆኗል። ሁል ጊዜም ለማጥቃት የማይሰንፈው አስራት ከኢትዮጵያ ቡና አጨዋወት ጋር ራሱን አስማምቶ በሜዳው ቁመት ካሉት የቡድን አጋሮቹ ጋር በመናበብ አብዛኛውን ጊዜውን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ በማሳለፍ የቡድኑን የግራ ወገን የማጥቃት ሂደት ሲያቀላጥፍ ዓመቱን አሳልፏል። ቦታውን ያለተቀናቃኝ አስከብሮ በጨረሰበት የውድድር ዓመትም በ23 ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል። እስከ ተጋጣሚው የግብ ክልል ድረስ አዘውትሮ መገኘት መቻሉም ከተከላካይ ቦታ በመነሳት ሦስት ግቦችን እንዲያስቆጥር ያገዘው ሲሆን አምስት ወደ ግብነት የተቀየሩ ኳሶችንም ማመቻቸት ችሏል።
አማካዮች
ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ
እንደ ቅፅል ስሙ (ጎላ) ሁሉ መሐል ሜዳ ላይ ጎልቶ የሚታየው ቀጭኑ አማካይ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑን ከፍታ የጨመረበትን የውድድር ዓመት አሳልፏል። በ18 ጨዋታዎች ቀዳሚ ተመራጭ የነበረው ሀብታሙ በግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አያድርግ እንጂ በቡድኑ አጨዋወት ውስጥ በብቸኛ የተከላካይ አማካይነት በተሰየመባቸው ጨዋታዎች በግሉ ባለው ጠንካራ ጎን ላይ ተመስርቶ ኃላፊነቱን በወግባቡ ተወጥቷል። እምብዛም ኃይል ባልቀላቀለ አጨዋወት የተጋጣሚዎቹን ኳስ በማስጣል ለተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች ጥሩ ሽፋን በመስጠት ፣ ከኋላ ክፍሉ ጋር በመናበብ ቡድኑ ኳስ መስርቶ ከራሱ ሜዳ እንዲወጣ በማስቻል እና ከኳስ ጋር በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ጥሩ አፈፃፀም በማሳየት ከአጥቂ አማካዮቹ ጋር ቅብብሎችን በመከወን የቡድኑ የማጥቃት ጥረት ክፍተቶችን እንዲያገኝ በማስቻሉ ረገድ አጥጋቢ እንቅስቃሴ አድርጓል።
ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ
እንደ ቡድን የባህር ዳር ከተማ የውድድር ዓመት ወጣ ገባ የሚባል ዓይነት ቢሆንም ፍፁም በግሉ መጥፎ ቀን ያሳለፈበትን ጨዋታ ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው። አይደክሜው አማካይ በየጨዋታው በርካታ ጉሽሚያዎችን እያስተናገደ ከአሁን አሁን የረጅም ጊዜ ጉዳት አገኘው ተብሎ ቢጠበቅም 21 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። በድፍረት የተሞላበት አጨዋወት መገለጫው የሆነው ፍፁም ከተከላካዮች እና ከአማካዮች ጋር በሚያገናኙት ቅፅበቶች ሁሉ ባለማመንታት በመፋለም የባህር ዳር ከተማ ዋነኛ የማጥቃት አማራጭ ሆኖ አገልግሏል። በተጋጣሚው አጋማሽ በሁሉም አቅጣጫዎች የመንቀሳቀስ ፍቃድ የነበረው አማካዩ በእንቅስቃሴ ለሌሎች የቡድን አጋሮቹ ይፈጥር ከነበረው ክፍተት በተጨማሪ ለግብ ቀርቦ በሚያደርገው እንቅስቃሴ 10 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በላይኛው የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ፉክክር ውስጥ የነበረ ብቸኛው የአማካይ ክፍል ተጫዋች መሆን ችሏል።
ታፈሰ ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና
አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ በቡድናቸው ለመተግበር በሚፈልጉት አጨዋወት ውስጥ ወሳኝ በሆነው አማካይ ክፍላቸው ላይ አብዝተው የተጠቀሙት ተጫዋች ታፈሰ ሰለሞን ነው። ተጫዋቹ ሜዳ ላይ ያለው ታታሪነቱ ጨምሮ በታየበት በዚህ የውድድር ዓመት ከተለያዩ አማካዮች ጋር በመጣመር የቡና የማጥቃት ሂደት ዋና አቀናባሪ ሆኖ ታይቷል። ቡድኑ በሚከውናቸው በርካታ ቅብብሎች ውስጥ በአመዛኙ ተሳታፊ የሆነው ታፈሰ የማጥቃት አቅጣጫዎችን በመወሰን እና የኳስ ፍሰቱን በማደራጀት እስከ ተጋጣሚ ሳጥን ድረስ ሲዘልቅ ይታያል። ክፍተት የማይሰጡ ተጋጣሚዎች ሲኖሩም በጥልቀት ወደ ኋላ እየተሳበ ጨዋታ የማንበብ ክፍሎቱን በመጥቀም መካከለኛ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ እንዲሁም ቅብብሎችን በማስጀመር ቁልፍ ሚና ነበረው። በዚህ ሂደት በውድድር ዓመቱ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የአጥቂ አማካዩ ስድስት ግብ የሆኑ ኳሶችንም ማመቻቸት ችሏል።
አጥቂዎች
ሽመክት ጉግሳ – ፋሲል ከነማ
በማጥቃት እና በመከላከል ሂደት ውስጥ ሰፊ የሜዳ ክፍል በመሸፈን በታታሪነት ዓመቱን ሙሉ በመጫወት ረገድ ሽመክትን የሚመጥን ሌላ ተጫዋች ማግኘት ከባድ ነው። ከእንቅስቃሴው ውጪም ሜዳ ላይ የሚታይበት ከፍተኛ ተነሳሽነት ከእርሱ አልፎ ለቡድን ጓደኞቹም ብርታት የሚሆን ነው። በአመዛኙ በቀኝ መስመር አጥቂነት ዓመቱን ያሳለፈው ሽመክት ፋሲል ከነማ በዚህ አቅጣጫ እጅግ አስፈሪ እንዲሆን ምክንያት ነበር። በሜዳው ቁመት ያለድካም እንደልብ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የተጋጣሚን የግራ መስመር ማጥቃት በማፈን እና ወደ ፊት ሲሄድ ደግሞ ወደ ሳጥን ውስጥ የጎንዮሽ ሩጫዎችን በመከወን ክፍተቶችን ሲፈጥር ታይቷል። ሽመክት በዓመቱ ሦስት ግቦችን ብቻ ያስቆጥር እንጂ 11 ግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት በሊጉ ቀዳሚው ተጫዋች መሆን ችሏል።
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
በ29 ግቦች የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያገባደደው አቡበከርን ለማወደስ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቃላትን ማግኘት ሳያስቸግር አይቀርም። በአብዛኛው ከመሀል አልፎ አልፎ ደግሞ ከግራ በመነሳት የማጥቃት ኃላፊነት ይሰጠው የነበረው ተጫዋቹ የቡና ሁሉ ነገር ሆኖ ዓመቱን ጨርሷል። በሊጉ ከአቡበከር በላይ ጎል ያላቸው ክለቦች የራሱን ቡድን ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ አምስት ብቻ መሆናቸው ወጣቱ አጥቂ ምን ያህል ርቆ እንደሄደ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በተለይም ቡና ሁለተኛ ሆኖ ለመጨረስ በታገለባቸው ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ላይ በተሰረጉት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች ቡድኑ ካስቆጠራቸው 11 ግቦች አስሩን ከመረብ ማሳረፍ መቻሉ የእርሱ መኖር ለቡና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ መሳካት የነበረውን አስተዋፅዖ በግልፅ የሚያሳይ ነበር።
ሙጂብ ቃሲም – ፋሲል ከነማ
ሙጂብ የቻምፒዮኖቹን ስብስብ በብቸኛ አጥቂነት የመራባቸው ጨዋታዎች እጅግ በርካታ ናቸው። በጥቅሉም በ 23 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል። የሰጠ ተክለሰውነት ባለቤት የሆነው አጥቂው የአየር ላይ ኳሶችን በመግጨትም ሆነ በእግር በሚቆጠሩ ኳሶች ቡድኑ ወደ ዋንጫው ያደርግ የነበረውን ጉዞ አግዟል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ሙጂብ 20 ግቦችን ከመረብ አገናኝቶ የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፋሲል ከነማ በስምንት ጨዋታዎች በሙጂብ ጎሎች ብቻ 24 ነጥቦችን መስብሰብ መቻሉ ነው። ግዙፉ አጥቂ ሦስት ጎል የሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት ሲችል የቡድኑ ፊት አውራሪ መሆኑ ተግማች ሆኖ እንኳን ተጋጣሚዎቹ ሊያቆሙት ተቸግረው ዓመቱን ማገባደዱ የአጥቂነት ብቃቱን ያሳየ ነበር።
የዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ
ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ፋሲል ከነማን ለቻምፒዮንነት ክብር ያበቁት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በማያከራክር መልኩ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ናቸው። የተረጋጋ እና ብዙ ለውጦች የማይታይበትን ቡድን መገንባት የቻሉት አሰልጣኙ 4-2-3-1 እና 4-1-4-1ን እንደሁኔታው በመጠቀም ቡድናቸው በጥንካሬው እንዲዘልቅ እና ባለ ድል እንዲሆን አስችለውታል። ከዚህ ባለፈ በዚህ ዓመት ወደ ክለቡ የመጡ ተጫዋቾችን ይየቀደመ ጥንካሬውን በማይነካ መልኩ እንደአስፈላጊነቱ በአግባቡ በመጠቀም ለወጣት ተጫዋቾችም ዕድል በመስጠት የቡድን መንፈሱን ጠብቀው ዳር አድርሰውታል።
የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች
አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ ካስቆጠራቸው ግቦች 66% የሚሆነውን ከመረብ ያገናኘው አቡበከር ናስርን የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች አድርገን መርጠነዋል። ከግቦቹ ባሻገር ወደ ኋላ ተስቦ ለአማካይ ክፍሉ ቀርቦ በመጫወት እና ክፍተቶችን በመፍጠር ጥሩ የቡድን ተጫዋች በመሆን እና በተወሰኑ ጨዋታዎች በአምበልነት በመምራት ዓመቱን አሳልፏል። ቡና ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች ውስጥ ግብ ቀንቶት ከሜዳ በወጣባቸው ጊዜያት አጥቂው ሜዳ ላይ ሆኖ ኳስ እና መረብን ሳያገናኝ የቀረው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በአጠቃላይ የዘንድሮውን ኢትዮጵያ ቡና ያለአቡበከር ናስር ግቦች ማሰብ ከባድ ይሆናል።
የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ
ሚካል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
(ስለ ግብ ጠባቂው የተሰጠውን ገለፃ ከላይ ይመልከቱ)
ተጠባባቂዎች
መሐመድ ሙንታሪ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ረመዳን የሱፍ (ወልቂጤ ከተማ)
ምኞት ደበበ (ሀዋሳ ከተማ)
በረከት ወልዴ (ወላይታ ድቻ)
ወንድማገኝ ኃይሉ (ሀዋሳ ከተማ)
ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)
ዳዋ ሆቴሳ (ሀዲያ ሆሳዕና)