ካሳለፍነው ዓመት አንስቶ ሲያነጋግር በቆየው የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂዎች ጉዳይ ዙርያ ውሳኔ ሊሰጥ ነው።
የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች በሊጋችን መብዛትን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች ብቃት መውረድ እና በስፋት የተሰላፊነት ዕድል ማጣት በተለይ በብሔራዊ ቡድኑ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ በመምጣቱ ከተለያዩ ወገኖች የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች አስፈላጊነት ሲያነጋግር ሰነባብቷል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የእግርኳሱ የበላይ አካል የሆነው ፌዴሬሽኑ በተለያዩ መድረኮች በ2012 ክረምት የ2013 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ ለክለቦች የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች ማሰለፍን የሚከለክል ረቂቅ በመበተን ምላሽ እንዲሰጡ ቢያደርግም በምን ሁኔታው ሀሳቡ እንደተቋጨ ሳይታወቅ የዘንድሮ ውድድር መጠናቀቁ ይታወቃል።
አሁን ደግሞ ዓመት ጠብቆ ይህ ርዕስ በድጋሚ እየተነሳ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ዙርያ ፌዴሬሽኑ ምን እያሰበ እንደሆነ ባገኘነው መረጃ መሠረት በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ፌዴሬሽኑ ያለውን አቋም አስመልክቶ የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ አስቀድሞ በደብዳቤ እንደሚያሳውቅ ሰምተናል።
ምን አልባትም የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂዎች የመቅረታቸው ነገር እየሰፋ እንደመጣ የተገነዘቡ አንዳንድ ክለቦች ለዓመታት በውጭ ግብጠባቂ ሲጠቀሙ የቆዩበትን ልማድ በመተው የሀገር ውስጥ ግብጠባቂ በቋሚነት ለመጠቀም ከወዲሁ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ለማወቅ ችለናል።