ለሴካፋ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበላቸው አምስት ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

በሴካፋ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ቡድንን እንደሚቀላቀሉ የተገለፀው የዋናው ቡድን አምስት ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑ መረጃ አግኝተናል።

በሰኔ ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የመካከለኛው እና ምስራቅ ሀገራት የእግር ኳስ ውድድር በባህር ዳር ከተማ እንደሚከወን ይታወቃል። ለዚህ ውድድር ይረዳ ዘንድ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ትናንት ምሽት ለ35 ተጫዋቾችን ጥሪ ማድረጋቸው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የተጫዋቾቹ ዝርዝር ሲወጣም ወደ አፍሪካ ዋንጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲያልፍ የቡድኑ አባላት ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ዕድሚያቸው በብሔራዊ ቡድኑ እንዲካተቱ የሚፈቅድላቸው 5 ተጫዋቾች ቡድኑ ልምምድ ከጀመረ ሰባት ቀናት በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን እንደሚቀላቀሉ ቢገለፅም ስማቸው በዝርዝር ይፋ ሳይሆን ቀርቷል። ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ግን በሂደት የሚቀየር ነገር ካልኖረ በቀር አምስቱ ተጫዋቾች ምንተስኖት አሎ (ሰበታ ከተማ)፣ ረመዳን የሱፍ (ወልቂጤ ከተማ)፣ ሀብታሙ ተከስተ (ፋሲል ከነማ)፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል (ቅዱስ ጊዮርጊስ) እና አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና) መሆናቸውን አረጋግጣለች።

በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ፍቅሩ ወዴሳ እና ሰለሞን ወዴሳ እንዲሁም አቡበከር ናስር እና ሬዲዋን ናስር ከአንድ ቤተሰብ የተገኙ ወንድማማቾች መሆናቸው ስብስቡን የተለየ ያደርገዋል።