የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በራሱ ስም ለታዳጊዎች የሚሆኑ ትጥቆችን በራሱ አቅም ለማምረት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በየክልሉ እና ከተማዎች ላይ የተደራጀ የታዳጊዎች ስልጠና እና ውድድር ለማከናወን እንቅስቃሴእያደረገ የሚገኝ ሲሆን በሀገሪቱ የሚገኙ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ተቋማት እና ፕሮጀክቶች የመለማመጃም ሆነ የመጫወቻ መለያዎች ችግር እየገጠማቸው በመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ በራሱ አቅም ትጥቅ ሊያመርት ተዘጋጅቷል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረትም ፌዴሬሽኑ ትጥቆቹን ለማምረት የሚረዱ የመስፊያ ማሸኖች፣ የቁጥር መፃፍያ መሳሪያዎች እና ሌሎች መለያ እና ቁምጣን የሚያመርቱ ማሽኖችን እየገዛ ሲሆን ቀሪዎቹን በሟሟላት በቅርቡ ባለሞያዎችን ቀጥሮ ወደ ማምረቱ እንደሚገባ ሰምተናል፡፡ የመጫወቻ ኳሶችን በቀጣይ በራሱ ለማምረት በዝግጅት ላይ ይገኛልም ተብሏል፡፡
ይህ እርምጃ በሀገሪቱ የሚገኙ የማሰልጠኛ ማዕከላት መሠረታዊ ችግር የሆነው የትጥቅ ዕጥረት እንደሚቀርፍ ሲታሰብ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም ለግዢ የሚያወጣው ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ታምኖበታል።