የፈረሰኞቹ አጥቂ ቀዶ ጥገና አከናውኗል

ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት ከሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰው አዲስ ግደይ በዛሬው ዕለት የቀዶ ጥገና ህክምና ማከናወኑ ሲታወቅ ከሜዳ የሚርቅበትም ጊዜ ተገልጿል።

በሲዳማ ቡና ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የተጫወተው አዲስ ግዳይ ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት ስሙን የተከለበትን ክለብ ለቆ የመዲናውን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተቀላቅሎ ነበር። እንደታሰበው በቅዱስ ጊዮርጊስ የተሳካ ቆይታ ያላሳለፈው አጥቂው ከወራት በፊት ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሲያከናውን የጉልበት ጉዳት አስተናግዶ ነበር። በዘንድሮ የውድድር ዘመን 12 ጨዋታዎችን (6 በመጀመሪያ ተሰላፊነት) የተጫወተው አጥቂው ከቀድሞ ክለቡ ጋር ሲጫወት ጠንከር ያለ ጉዳት ካስተናገደ በኋላ ወደ ሜዳ ሳይመለስ ቀርቷል። በፕሪምየር ሊጉም ከባህር ዳሩ የውድድር ምዕራፍ በኋላ በዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ ያልተሳተፈው አጥቂው በዛሬው ዕለት የተሳካ የቀዶ ጥገና ህክምና ማድረጉ ተገልጿል።

ክለቡ ከደቂቃዎች በፊት በፌስ ቡክ ገፁ እንዳስታወቀው ከሆነ በማርሻ የህክምና ማዕከል ለግማሽ ቀን የፈጀ ቀዶ ጥገና ማድረጉን ተገልጿል። በመረጃው ላይ እንደተመላከተው ከሆነም አዲስ ሙሉ በሙሉ ከህመሙ አገግሞ ወደ ሜዳ ለመመለስ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ሊፈጅበት እንደሚችልም የህክምና ባለሙያዎች መግለፃቸውም ተብራርቷል።