የ2014 ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦችን በተመለከተ ውሳኔ ተላለፈ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2014 ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዎችን ለመለየት ከወዲሁ የመለያ ጨዋታ አድርገው ከአንድ እስከ ሦሰት የሚወጡ ክለቦች የትግራይ ክልል ክለቦች መሳተፍ አለመሳተፍን እንዲጠባበቁ ውሳኔ አሳልፏል።

ፌዴሬሽኑ ያወጣው ሙሉ መረጃ ይህንን ይመስላል:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ ሰኔ 1/2013 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ የተለያዩ ውሳኔዎችን ወስነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከትግራይ ክልል ክለቦች እና ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ውይይት ያካሄደ ሲሆን ክለቦቹም ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታን በማስረዳት በ2014 የውድድር ዘመን የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳወቁ ሲሆን የፋይናንሱ ጉዳይ እንደሚያስቸግራቸው በማስረዳት በቀጣይም ከክለብ የበላይ አመራሮች እና ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋገር የመጨረሻ ውሳኔያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያሳውቁ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ በፌዴሬሽም የክለቦቹ ውሳኔ እየተጠባበቀ ሁለተኛ አማራጭ ውሳኔ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በቀጣይ በመወሰን እንደሚያሳውቅ ከስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ሰኔ 1/2013ዓ.ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልል የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የክለቦች የምዝገባ ወቅትን ጠብቀው የማይመዘገቡ እና የማይሳተፉ ከሆነ ሌላ አማራጭ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ ከዚህ የሚመከተለውን የዉሳኔ አማራጭ አስተላልፏል።

1ኛ. በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሊጉ ደረጃ ግርጌ የሚገኙት ወራጅ ክለቦች ከ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድር በሶስቱም ምድቦች 2ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ ክለቦች የነጥብ የአንድ ዙር ውድድር በማድረግ የተሻለ ነጥብ የሚያስመዘግቡ በደረጃ ከ 1ኛ እስከ 3ኛ ሆነው የሚያጠናቅቁ ቡድኖች የትግራይ ክልል የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተሳትፎን የሚጠባበቁ ይሆናል።

2ኛ. የትግራይ ክልል ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ የክለቦች የምዝገባ ጊዜን ጠብቀው ሙሉ በሙሉ የሚሳተፉ ከሆነ በሁለተኛ አማራጭነት የቀረበው ሀሳብ ቀርቶ የትግራይ ክልል ክለቦች ተሳታፊ ይሆናሉ።

3ኛ. የትግራይ ክልል ክለቦች ሙሉ በሙሉ የማይሳተፉ ከሆነ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በወሰነው መሰረት በነጥብ ውድድር ተሳትፈው ከ1-3 የወጡት ክለቦች በ2014 የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የትግራይ ክልል ክለቦችን ተክተው የሚወዳደሩ ይሆናል።

4ኛ. ከትግራይ ክልል ክለቦች 1 ወይም 2 ክለብ በሊጉ ለመሳተፍ የሚመዘገብ እና ሌሎች የማይሳተፉ ከሆነ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በወሰነው መሰረት በነጥብ ውድድር ተሳትፈው ከ1-3 ከወጡት ክለቦች መካከል የተሻለ ነጥብ ያስመዘገበው በቅደም ተከተል በፕሪሚየር ሊጉ እንዲሳተፍ ይደረጋል።

ይህ ውድድር የፊታችን ሰኔ 18/2013ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ መካሄድ ይጀምራል።

– በ2013 የኢትዮጵያ የቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ወራጅ የነበሩ ሶስት ክለቦች በከፍተኛ ሊጉ ከየምድቡ 2ኛ ደረጃን በመያዝ ካጠናቀቁ ክለቦች ጋር የነጥብ ውድድሩን ያካሂዳሉ።

– በከፍተኛ ሊግ 2ኛ ደረጃን ይዘው ካጠናቀቁ ክለቦች በተለያዩ ምክንያቶች መሳተፍ የማይችል ክለብ በሌላ ክለብ ሳይተካ ባሉት ክለቦች ውድድሩ ይካሄዳል።

– በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ክለቦች የሚያሰልፏቸው ተጫዋቾች በ2013 በክለቡ ቲሴራ የተመዘገቡ ብቻ ይሆናሉ።