በሻላ እግርኳስ ማኅበር አዘጋጅነት የቀድሞው ታላቅ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬን የሚዘክር ውድድር ሃያ ሁለት በሚገኘው የሻላ ሜዳ መካሄድ ጀምሯል።
የዛሬ አራት ዓመት በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ መድን እና ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬን ለማሰብ በስምንት ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍሎ በዛሬው ዕለት በሻላ ሜዳ የመክፈቻ መርሀግብሩን አድርጓል።
በዕለቱ የስፖርት ጋዜጠኞች ከዲጄዎች ጋር ወዳጅነት ጨዋታ ካደረጉ በኃላ በመቀጠል ሻላ እግርኳስ ማኅበር ከ መነኻርያ እግርኳስ ማኅበር ጋር እጅግ ጠንካራ ፉክክር ያስተናገደ ጨዋታ አድርገው በመናኸሪያ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው አስረኛ ደቂቃም አሰግድ ተስፋዬ የሚለብሰውን አስር ቁጥር መለያ በማሰብ ጨዋታው እንዲቆም ተደርጎ የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
በማስከተል በኮተቤ እግርኳስ ማኅበር እና በኢትዮ አፍሪካ እግርኳስ ማኅበር መካከል የተካሄደው ጨዋታ በኢትዮ አፍሪካ 3–1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዚህ ትልቅ አላማ በነገበ ውድድር የቀድሞ ድንቅ ተጫዋቾች አዳነ ግርማ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ምንያህል ተሾመ፣ ታፈሰ ተስፋዬ፣ አሉላ ግርማ፣ ውብሸት ደሳለኝ፣ ፍፁም ተፈሪ፣ አብዱልከሪም ሀሰን (ምርምር)፣ መንግሥቱ አሰፋ (ማሲንቆ) እና ሌሎች ከዋክብቶች ተሳታፊ ሆነውበታል።
ይህ ሊለመድ የሚገባው በእግርኳሱ አሻራ ጥለው ያለፉ ኮከቦችን የማስታወስ ተግባር ለአንድ ሳምንት በሻላ ሜዳ ሲካሄድ ቆይቶ ሰኔ 12 ቀን ፍፃሜውን የሚያገኝ ይሆናል።