የቡና ኃላፊዎች የውድድር ዓመቱን ሪፖርት እና ክለቡ ከ ‘ከ ሀ እስከ ፐ ‘ ጋር ስላደረገው አዲስ የሥራ ስምምነት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዛሬ ከሰዓት በስካይ ላይት ሆቴል የተሰጠው የኢትዮጵያ ቡና ጋዜጣዊ መግለጫ ሦስት ክፍሎች ነበሩት። በቀዳሚነት አስተዳደራዊ እና ቴክኒካዊ ሪፖርቶች በሥራ አስኪያጁ አቶ ገዛሀኝ ወልዴ እና በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አማካይነት ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ክለቡ ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ ከተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት ጋር ያደረገው ስምምነት ይፋ ተደርጓል።
አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የተመለከተው የአቶ ገዛኸኝ ማብራሪያ ከዝውውር ጊዜ አንስቶ እስከ ውድድሩ ማብቂያ ያነበሩ ሁነቶችን የተመለለከተ ነበር። ሥራ አስኪያጁ ክለቡ ከአሰልጣኝ ቡድኑ ጋር በመናበብ ስለሰራቸው ረጅም የኮንትራት ማራዘም ሥራዎች እና አዲስ ተጫዋቾችን የማስፈረም ሂደት እንዲሁም በውድድሩ በየከተማዎቹ ስላስመዘገበው ውጤት በማብራራት ሪፖርታቸውን ጀምረዋል። ከሌሎቹ ከተሞች በተለየ ውጤቱ በወረደበት የድሬዳዋው ውድድር የመጫወቻ እና የልምምድ ሜዳ ምቹ አለመሆን እንዲሁም የኮቪድ የምርመራ ሂደት መዛባት ስላሳደረባቸው ጫናም ተናግረዋል። ክለቡ በስፖንሰርሺፕ አብረውት እየሰሩ ካሉ ድርጅቶች ካገኘው ገቢ ውስጥ ለተጫዋቾ ከ 3.3 ሚሊዮን ለአሰልጣኞች ደግሞ ከ 260 ሺህ ብር በላይ ለደመወዝ እና ለጥቅማጥቅም በየወሩ ወጪ ማድረጉም በሪፖርቱ ተካቷል። አስተዳደሩ ረጃጅም ኮንትራቶችን ማስፈረሙ ፣ ቡድኑ ደረጃቸውን በጠበቁ ሆቴሎች በየከተማው እንዲያርፍ ማድረጉ ፣ የዲስፕሊን እርምጃዎች መወሰናቸው ፣ አመራሮች በውድድር ቦታ መገኘታቸውን እንዲሁም የካምፕ እና የልምምድ ሜዳውን ሥራ ላይ ማዋሉን በጠንካራ ጎንነት ሲያነሳ የዲስፕሊን ችግር በተደጋጋሚ መታየቱ ፣ የኮንትራት ማራዘሙ ሂደት በጀመረው ፍጥነት አለመቀጠሉን በደካማ ጎንነት አንቀምጧል።
በመቀጠል የቀረበው የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ሪፖርት በቡድኑ አጨዋወት ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር። ቡድኑ የመጫዋቻ ቦታዎችን እና ነፃ ሰዎችን በማግኘት ሂደቱን እስከተጋጣሚ ጎል ድረስ ብበመቀጠል 90 ደቂቃ ለመንቀሳቀስ በሚያደርገው ጥረት በተጋጣሚዎች ተገማች ስለመሆኑ ያነሱት አሰልጣኝ ካሳዬ ያ መሆኑ የተጋጣሚዎቻቸውንም አመጣጥ ስለሚያሳያቸው በራሱ እንደችግር እንደማያዩት ጠቁመዋል። ምርጫቸው ያደረጉትን አጨዋወት በመተግበር ውስጥ ይታዩ የነበሩ ግለሰባዊ ስህተቶች አጨዋወቱን የሚያስቀይሩ ባለመሆናቸው ከተጫዋቾች ጋር በተግባር እና በመነጋገር እያረሙ ለመሄድ መሞከራቸውን አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተጫዋቾች ስለአጨዋወቱ ግንዛቤው ኖሯቸው በሥነ ልቦናው ረገድ ጠንክረው ወደ ሜዳ እንዲገቡ በማድረጉ ረገድም መሰራቱን አስረድተዋል።
በመቀጠል በሪፖርቶቹ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ከሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪ መቶ አለቃ ፋቃደ ማሞ ምላሾችን ሰጥተዋል። ከተሰጡት ምላሾች ውስጥ ሥራ አስኪያጁ በረጅም ጊዜ ኮንትራቶች ውስጥ የተጫዋቾች እና የክለቡ ጥቅሞች በስምምነት የተቀመጡ ስለመሆኑ ፣ ክለቡ በየዓመቱ ከ 15-20% የበጀት ጉድለት እየገጠመው ስለመሆኑ እና በቀጣይ ዓመት አህጉራዊ ውድድር የሚጠብቀው በመሆኑ ለተጨማሪ በጀት እንድሚሰሩ ፣ በዘንድሮው ውድድር በየከተማው ለሆቴል በከ 4.3 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ስለማውጣቱ አንስተዋል። በዚህ ላይ ሀሳባቸውን ያከሉት መቶ አለቃ ፍቃደ ደግሞ የክለቡ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ በ 2014 ውድድር ወቅት ያለመጫወቻ ሜዳ እንዳትቀር ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል።
ለሜዳ ላይ ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት አሰልጣኝ ካሳዬ በበኩላቸው በቀጣይ ዓመት ሜዳ ላይ የታዩ ስህተቶችን በብዙ ቀንሶ በመገኘት ለቻምፒዮንነት እንደሚጫወቱ ፣ ተጫዋቾች የአጨዋወት ሂደቱን መጠበቅ ፣ ራስን ለቅብብል በማዘጋጀት እና የመጨረሻ ኳስ በማድረስ የተሻሉ እንዲሆኑ እንደሚሰሩ ሲገልፁ ቡድኑ ግቦችን ለማግኘት በአቡበከር ላይ መመስረቱ እምብዛም እንደማያሳስባቸው ከዛ ይልቅ ለአቡበከር ዕድሎችን የፈጠረው የቡድን ሥራው የሚቀጥል ከሆነ በአንድ ተጫዋች ላይ መመስረቱ ችግር ላይኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል። አሰልጣኙ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቡበከር ከክለቡ ጋር ቢለያይ እሱ በመጣበት መንገድ ሌላ ተጫዋች እንደሚያበቁ ያላቸውን ዕምነት ገልፀዋል።
ቀጣዩ የዕለቱ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ‘ከ ሀ እስከ ፐ’ ከተባለው የማስታወቂያ ድርጅት ጋር ያደረገው ስምምነት ነው። የ ከ ሀ እስከ ፐ አመራር የሆኑት አቶ ፍሬዘር አብይ ስለድርጅታቸው እና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ስለሚኖረው የሥራ ግንኙነት ተናግረዋል። በዚህም የማስታወቂያ ድርጅታቸው የኢትዮጵያ ቡና አርማ የታተመባቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ለሽያጭ የሚቀርቡባቸው ሱቆችን በመክፍፈት ፣ ዕቃዎችን በማምረት እና በማስተዳደር ከክለቡ ጋር እንደሚሰራ አብራርታዋል።
በጉዳዩ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ተወካዮች በተሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያም ድርጅቱ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የቡና አርማ በቁሳቁሶች በኩል ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ እንዲሁም ሱቆቹ በአዲስ አበባ በተመረጡ ሁለት ቦታዎች ተጀምሮ በ ከ ሀ እስከ ፐ ወጪ እንደሚመሰረቱ ተናግረዋል። ከሽያጭ ባለፈ የካፌ አገልግሎት ይኖረዋል የተባለው ሱቅ በሂደት ወደ ኦንላይን ሽያጭ እና ፈረንቻይዝ አሰራሮችም እንደሚያድግ ሲጠቆሙ ክለቡ በዚህ ሂደት ውስጥ ብራንዱን ከማሳደግ ባለፈ በ20% የባለቤትነት ክፍያ እና በ20% ደግሞ ከትርፍ ላይ በመካፈል በፋይናንስም ተጠቃሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።
በመጨረሻም በክለቡ እና በማስታወቂያ ድርጅቱ መሀከል ስምምነቱ ተፈርሞ መርሐ ግብሩ ተቋጭቷል።