ኢትዮጵያ ቡና የዕውቅና እና ሽልማት ፕሮግራም አካሄደ

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዋናው የወንዶች ቡድኑ ወደ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ማለፉን በመንተራስ እንዲሁም በሌሎች ቡድኖቹ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ኮከቦቹ በስካይ ላይት ሆቴል የዕውቅና አሰጣጥ መርሐግብር አካሄዷል።

ከምሽቱ አስራ አንድ ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው በዚህ የዕውቅና ፕሮግራም ላይ የመዲናችን ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ የቀድሞ ርዕሰ ብሔር እና የኢትዮጵያ ቡና የበላይ ጠባቂ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የቡና ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

በቅድሚያ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ” ቡና ከምስረታው ጀምሮ አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ አሁን ለስኬት እዚህ ደረጃ ደርሷል። በተለይ ያለፉትን ሁለት ዓመታት የክለቡን አቅም ለማሳደግ ፈርጀ ብዙ ስራዎችን ስንሰራ እንደነበር ይታወቃል። በቀጣይም የክለቡን አቅም ከፍ ላማድረግ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት አቅደን እየሠራን ነው።” ብለዋል።

በማስከተል የከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በዚህ ዝግጅት በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ኢትዮጵያ ቡና በሀገሪቱ ከሚገኙ ክለቦች ተወዳጅ መሆኑን አውስተዋል። ከንቲባዋ አክለውም ቡና ለብዙ ወጣት ታዳጊዎች ተምሳሌት የሆነ ክለብ በመሆኑ የከተማው አስተዳደር ክለቡን ለማጠናከር ካስረከበው መሬት በተጨማሪ ክለቡን ለማገዝ ቁርጠኛ መሆኑን አበክረው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ለክብርት አዳነች አበቤ የቡና አስራ ሁለት ቁጥር ማልያ በስማቸው የታተመበት ስጦታ አበርክተውላቸዋል። እንዲሁም ለአቶ ዣንጥራር ዓባይ የክለቡ አርማ ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም ለክለቡ የበላይ ጠባቂ በመሆን እያገለገሉ ለሚገኙት የቀድሞ ፕሬዝደንት ክቡር ሙላቱ ተሾመ በተመሳሳይ የቡና አስራ ሁለት ቁጥር ያረፈበት እና ስማቸው ያለበት ማልያ አበርክተውላቸዋል።

የዕለቱ የእውቅና ፕሮግራም በተለያዩ የመክፈቻ ንግግሮች ከተጠናቀቀ በኃላ በሁሉም ዘርፍ አስታዋፅኦ ላደረጉ ተጫዋቾች የሐበሻ ወርቃማው የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት በተለያዩ የክብር እንግዶች አማካኝነት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

በዚህም መሠረት

በሴቶች ኮከብ ተጫዋች – ፍቅርተ ኃይሉ

ከ17 ዓመት በታች ኮከብ ተጫዋች – ሱራፌል ሰይፉ

ከ20 ዓመት በታች ኮከብ ተጫዋች – ሙሴ ከበላ

ልዩ ተሸላሚ – አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ

ኮከብ ተጫዋች – አቡበከር ናስር የልዩ ዋንጫ እና ሱዝኪ 2021 መኪና ተሸልሟል።

ሐበሻ ቢራ ለሁሉም ቡድኑ አባላት 900,000,00 እንዲሁም ለተጫዋቾቹ የማበረታቻ ጥቅማጥቅም 910,485,00 ብር በሽልማት መልክ አበርክቷል።

በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ቡና ለአስርት ዓመታት ከምስረታው እስከ አሁን በሀዘኑም በደስታውም ከክለቡ ጎን በመቆም ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ልዩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ለሌሎች ክለቦች ዓርአያ በሚሆን መልኩ የተካሄደው በዚህ የእውቅና ምሽት አሰጣጥ በቀጣይም መለመድ ያለበት መሆኑን እናስገነዝባለን።