አርባምንጭ ከተማ የአሰልጣኙን ኮንትራት አድሷል

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በአርባምንጭ ከተማ ውላቸውን አራዝመዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ ከሦስት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ 2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን የምድብ ሐ ውድድርን ሳይሸነፍ በበላይነት አጠናቆ ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ ክለቡ ለከርሞ በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ይችል ዘንድ እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን አስቀድሞ ግን የአሰልጣኙን ኮንትራል ማደስን ቀዳሚው ተግባሩ አድርጓል፡፡

ከ2011 ጀምሮ ክለቡን ያሰለጠኑት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለአንድ ተጨማሪ ዓመት በክለቡ መቆየታቸው ዕርግጥ ሆኗል፡፡ “በክለቡ በምቆየው ደስተኛ ስለሆንኩ ነው። አመራሩም በእኔ እምነት አለው። በሁሉም ነገሮች ደስተኛ ነኝ።” በማለት ስለውል ማራዘማቸው በአጭሩ ነግረውናል፡፡

ወላይታ ድቻን ልክ እንደ አርባምንጭ ሁሉ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ እስከ 2010 አጋማሽ ድረስ ቆይታ የነበራቸው አሰልጣኙ ፋሲል ከነማንም አሰልጥነው ካለፉ በኃላ ነበር ወደ አዞዎቹ ቤት ያቀኑት፡፡

ያጋሩ