የሀዲያ ሆሳዕና እና የአስራ አምስቱ ተጫዋቾች ጉዳይ ውሳኔ አገኘ

በአስራ አምስቱ ተጫዋቾች እና በሀድያ ሆሳዕና ክለብ መካከል የተፈጠረውን ክርክር ሲመለከት የቆየው ፌዴሬሽኑ በዛሬው ዕለት ውሳኔ ሰጥቷል።

የማትጊያ ገንዘብ ክለቡ በሰጠን ማረጋገጫ መሠረት ይክፈለን በማለት አስራ አምስት ተጫዋቾች ለወራት ያቀረቡት ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ ምክንያት ከልምምድም ሆነ ከጨዋታ ራሳቸውን ማግለላቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ክለቡ በወሰደው የዲሲፕሊን እርምጃ ተጫዋቾቹን ለሁለት ዓመት ማገዱም ይታወቃል።

ተጫዋቾቹ ክለቡ የወሰነብን ውሳኔ ተገቢ አይደለም። ቅሬታችንን ተመልክቶ የእግርኳሱ የበላይ አካል መፍትሔ ይስጠን በማለት ያስገቡትን ደብዳቤ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሲመለከተው የቆየ ሲሆን በዛሬው ዕለት ውሳኔ አሳልፏል።

በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሠረት ክለቡ ከወራት በፊት በ15ቱ ተጫዋቾች ላይ ያሳለፈው የሁለት ዓመት ዕግድ ሙሉ ለሙሉ የተሻረ ሲሆን ክለቡ በሌላ መንገድ ልዩነታቸውን የመፍታት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጫዋቾቹ ወደ ወደ ክለቡ እንዲመለሱ ተወስኗል። ከሁለቱ ወገኖች አንደኛው ወደ ሥራ የመመለስ ፍቃደኝነት ካላሳዩም እስከ ውላቸው መጨረሻ ያለውን ደሞዛቸውን ክለቡ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፏል።

ከዕግድ መሻር ውሳኔው በተጨማሪ በተጫዋቾቹ እና በክለቡ መካከል ሚያዚያ 5 በተደረገው ስምምነት ላይ የተገለፁት የማትጊያ ክፍያዎችን በ7 የሥራ ቀናት ውስጥ እንዲከፈላቸው ሲወሰን ክፍያውን በተጠቀሱት ቀናት ካልፈፀመ ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከሊግ ካምፓኒው ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ እና ከውድድርም እንዲታገድ ወስኗል። ተጫዋቾቹም ክፍያ በተፈፀመላቸው በአምስት ቀናት ውስጥ ለማስያዣነት የተቀበሉትን የባንክ ቼክ ለክለቡ እንዲመልሱ ውሳኔ ተወስኗል።

ከአስራ አምስቱ ተጫዋቾች ጋር ከተያያዘው ውሳኔ በተጨማሪ ተስፋዬ በቀለ እና አልሀሰን ካሉሻ የመስከረም እና የጥቅምት ወር 2013 ክፍያን ለመክፈል የውል ስምምነት ያለው በመሆኑ ይህን ያልፈፀመ ክፍያን ክለቡ ለተጫዋቾቹ እንዲፈፅም ውሳኔ ማሳለፉን ለማወቅ ችለናል።

የፌዴሬሽኑ ውሳኔን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የይግባኝ ደብዳቤ ነገ ለፌዴሬሽኑ ሊያስገቡ እንደሆነ ከክለቡ አካባቢ ሰምተናል።

ያጋሩ