የጌዲኦ ዲላ ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ፍፃሜውን አግኝቷል

በጌዲኦ ዲላ ስፖርት ክለብ አስተናጋጅነት በጌዲኦ በ8 ዞን ከአምስቱም ከተማ አስተዳደር በተወጣጡ 16 ክለቦች መካከል ሲካሄድ የሰነበተው ከ17 ዓመት በታች ውድድር በተስፋ ስንቅ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ዛሬ በተከናወነው የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የጌዴኦ ዞን ባህልና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዩሴፍ ማሩ (ዕጬ ዶ/ር) እንዲሁም የክለቡ የቦርድ አባልና የዞኑ ዋና አስተዳደር ተወካይ በክብር እንግድነት ታድመዋል። “ተልዕኮአችን-በተግባራችን” በሚል ስያሜ በጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ አዘጋጅነትና በሰላም ሆስፒታል ስፖንሰር አድራጊነት በዲላ ሁለገብ ስታዲዮም ሲካሄድ የነበረው ውድድር 3 ሰዓት የደረጃ ጨዋታ በገደብ ከተማና በድል ባንቴ አካዳሚ መካከል ተደርጎበታል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አቅንቷል። በመለያ ምቱም የድል ባንቴ ቡድን የገደብ ከተማን 4ለ1 በመርታት በውድድሩ የሦስተኛ ደረጃን በማግኘት የነሃስ ተሸላሚ መሆን ችሏል። የዕለቱ ተጠባቂ እና የፍፃሜ የሆነው ጨዋታ በወናጎ ወረዳ እና ተስፋ ስንቅ መካከል ተደርጓል። ጨዋታውንም ተስፋ ስንቅ 3- 2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧዋል።

የውድድሩ አሸናፊ ለሆነው ቡድን (ተስፋ ስንቅ) የሜዳልያ እና የዋንጫ እንዲሁም ለዋናው ቡድን ተጫዋቾች እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘውን የፀባይ ዋንጫ ለከተማ አስተዳደሩ የማስረከብ በተጨማሪም ለኮከብ ተጫዋች እና ጎል አግቢ የሽልማት አሰጣጥ መርሐ-ግብር ተካሄዶል። በዚህም የውድድሩ አሸናፊ የሆነው የተስፋ ስንቅ ቡድን የዋንጫ እና የሜዳልያ ተሸላሚ፣ ውድድሩን በሁለተኛ ያጠናቀቀው የወናጎ ወረዳ ቡድን የብር ሜዳሊያና የውድድሩ የፀባይ ዋንጫ ተሻላሚ ሲሆን ሦስተኛ ደረጃ የያዘው የድል ባንቴ አካዳሚ ደግሞ የነሃስ ተሸላሚ ሆኗል። ከዚህ ውጪ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሳምሶን ታደሰ ከድል ባንቴ አካዳሚ ተመርጧል።

በተጨማሪ የጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ በ2013 የውድድር ዘመን የሁለቱንም የፆታ ቡድኑን ኮከቦች በመምረጥ ሽልማት የሰጠ ሲሆን በወንዶቹን የውድድር ዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ፋሲል አበባየሁ፣ በሴቶች ደግሞ እፀገነት ግርማ እንዲሁም የክለቡ የዓመቱ ከፍተኛ ጎል አግብ አልዓዛር ዘወዱ በመሆን ሽልማታቸውን ከክለቡ ፕሬዝዳንት ተቀብለዋል። በስተመጨረሻ በ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድር የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ የሆነው የጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የተሸለሙትን ዋንጫ ለክለቡ ፕሬዚዳንት እና ለዕለቱ የክብር እንግዳ አስረክበዋል።

በተያያዘ ዜና የጌዲዮ ዲላ ቡድን በቀጣይ የውድድር ዓመት ከ17 ዓመት በታች ቡድኑን ለውድድር እንደሚልክ ያገኘነው መረጃ ያመላልታል።