አስራ ሁለት ሀገራት ተሳታፊ እንደሚሆኑበት እና የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ የሚጠበቀው ከ23 ዓመት በታች የሴካፋ ዋንጫ ውድድር ከመካከለኛው አፍሪካ ተጋባዥ ሀገር አግኝቷል።
የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫ ካለፉት ዓመታት አንፃር ዘንድሮ በተለየ የዕድሜ ዕርከን ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 11 ድረስ በሀገራችን ኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይደረጋል፡፡ በውድድሩ ላይ ከ23 ዓመት በታች ዕድሜ ላይ የሚገኙ 11 የቀጠናው ሀገራት በውድድሩ ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን የሴካፋ ኮሚቴም ለሁለት ሀገራት የተጋባዥነት ጥያቄ አቅርቦ የመካከለኛው አፍሪካ ሀገር የሆነችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለመሳተፍ ይሁኝታዋን ሰጥታለች። በዚህም ውድድሩ በድምሩ በአስራ ሁለት ሀገራት መካከል በሦስት ምድቦች ተከፍሎ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
በውድድሩ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ዝግጅት እያደረገች የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ አስራ አንዱ የክፍለ አህጉሩ ሀገራት አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ተካፋይ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከሌሎቹ ሀገራት በተለየ መልኩ ግን ዩጋንዳ ከወራት በፊት በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ቡድኗን እንደምታሳትፍ ሰምተናል።
በተያያዘ ዜና የባህር ዳሩ ውድድር የምስል መብቱን በገዛው የታንዛኒያው የቴሌቪዥን ጣቢያ አዛም (Azam Tv) የሚተላለፍ ሲሆን ጣብያው የተወሰኑ የስርጭት መሳሪያዎችን ከአማራ ቴሌቪዥን የሚወስድ በመሆኑ ከአዛም ጋር በጥምረት ሆኖ የአማራ ቴሌቪዥን የሚያስተላልፍበት ዕድል የሰፋ መሆኑ ተሰምቷል።