ወልቂጤ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅመዋል በማለት ከወራት በፊት ከክለቡ አግልሏቸው የቆዩቱን ሦስት ተጫዋቾች ወደ ክለቡ መልሷቸዋል።
ፍሬው ሰለሞን ፣ ይበልጣል ሽባባው እና አዳነ በላይነህ “አላስፈላጊ ቦታ ተገኝተዋል” በማለት ወልቂጤ ከወራት በፊት ከቡድኑ ካምፕ እንዲገለሉ መወሰኑ ይታወሳል። ወልቂጤዎች በቅርቡ እንደ አማራጭ በቀረበው የዙር ውድድር ዳግም በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን ለማለምለም በአዲሱ አሰልጣኛቸው ጳውሎስ ጌታቸው እየተመሩ የሀዋሳ ዝግጅታቸው ማድረግ ከጀመሩ ሁለተኛ ቀን ሆኗቸዋል። ታዲያ ለወራት ከቡድኑ የተገለሉት ስማቸው ከላይ የተጠቀሱ ሦስቱ ተጫዋቾች የቡድኑ አቅም ለማጠናከር በመቀላቀል የሁለት ቀን ልምምድ ሰርተዋል።
በተጫዋቾቹ በኩል መጀመርያ ከቡድኑ እንዲገለሉ የተደረገበት መንገድ በምን ምክንያት እንደሆነ እና አሁን ዳግመኛ ወደ ቡድኑ የተመለሱበት ሁኔታ በምን አግባብ እንደሆነ ከክለቡ ሥራ አስኪያጅ እና ቡድን መሪ ጋር ዛሬ ወይም ነገ ውይይት እንደሚያደርጉ ሰምተናል። ውይይታቸውም ቡድኑን በሚጠቅሙበት አግባብ እና አብሮ በስምምነት መስራት ላይ ያተኮረ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ የተለየ ነገር ካለ ተከታትለን መረጃውን የምናደርሳቹሁ ይሆናል።