በሀዲያ ሆሳዕና እና በተጫዋቾቹ ውዝግብ ዙርያ ፌዴሬሽኑ ያስተላለፈውን ውሳኔ ክለቡ በመቃወም ቅሬታውን አሰምቷል።
ለወራት በዘለቀው የክለቡ እና አስራ አምስት ተጫዋቾች ውዝግብ ላይ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ በመስጠት ሆሳዕና ተጫዋቾቹ ላይ የወሰነውን የሁለት ዓመት ዕግድ በመሻር በውላቸው መሠረት ክፍያቸውን እንዲፈፅም መወሰኑ ይታወሳል። ይህን ተከትሎም ክለቡ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ ማስገባቱ ታውቋል።
ክለቡ ዛሬ ባስገባው አራት ገፆች ያሉት የቅሬታ ደብዳቤ ላይ ለውሳኔው የተመሠረተው ጭብጥ አግባብ ያልሆነ እና ለተጫዋቾች ያደላ ነው፤ ተጫዋቾች እንዲታገዱ የተወሰነው በክለቡ መተዳደርያ ደንብ መሰረት ሆኖ ህጋዊ እርምጃ ቢወስድም የዲሲፕሊን ኮሚቴው ከህግ ማዕቀፍ ውጪ የክለቡ ውሳኔ ያለአግባብ እንዲሻር አድርጓል፤ በገዛ ፈቃዳቸው ላልተገኙበት ጊዜ ክለቡ ገንዘብ መክፈል የማይገደድ ሆኖ ሳለ ክፍያ እንድንፈፅም መደረጉ አግባብነት የለውም፤ ክለቡ እስከ መጋቢት ወር ድረስ ደሞዝ እና ማትጊያ ክፍያ ፈፅሟል። ውሳኔው ተፈፃሚ ይሁን ቢባል እንኳ ላገለገሉበት እንጂ በገዛ ፈቃዳቸው በጨዋታ ላይ ላልተገኙበት ደሞዝ እና ማትጊያ በደፈናው ይከፈላቸው የሚለው ውሳኔ የአንድ ወገንን ብቻ ያማከለ በመሆኑ ይታረምልኝ ሲል ጠይቋል።
ክለቡ ባቀረበው አቤቱታ ማጠቃለያ ላይ በአስራ አምስቱ ተጫዋቾች ላይ የተወሰነው የዲሲፕሊን እርምጃ ህግ እና የውል አስገዳጅነትን የተከተለ በመሆኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴውን ውሳኔ በማሻር የክለቡ ውሳኔ እንዲፀና፤ በተጨማሪም ይህ ይግባኝ ተመርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ውሳኔ ታግዶ እንዲቆይ ጠይቋል።
የይግባኝ ደብዳቤ👇
የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ👇