የአፍሪካ ዋንጫው የመጨረሻዋ ተሳታፊ ሀገር ታውቃለች

በኮቪድ ውዝግብ ምክንያት ከተያዘለት ጊዜ እጅግ ተራዝሞ በዛሬው ዕለት የተከናወነው የሴራሊዮን እና የቤኒን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ከደቂቃዎች በፊት ተጠናቋል።

ከ2021 ወደ 2022 የተዘዋወረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች በአስራ ሁለት ምድብ ተከፋፍለው የምድብ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል። ከአንደኛው ምድብ አንድ ጨዋታ ውጪም ሁሉም ጨዋታዎች ተጠናቀው ወደ ካሜሩኑ ፍልሚያ የሚያቀኑ ብሔራዊ ቡድኖች ተለይተው ታውቀዋል። በምድብ አስራ ሁለት የሚገኙት ሴራሊዮን እና ቤኒን ግን ውዝግብ በተሞላበት ሁኔታ ጨዋታቸውን በተያዘለት ጊዜ ሳያደርጉ ቀርተው ነበር።

የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ካፍም በመጀመሪያ መጋቢት 21 በናሽናል ስታዲየም እንዲደረግ መርሐ-ግብር አውጥቶለት የነበረውን ጨዋታ በኮቪድ-19 ውዝግብ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲዘዋወር ወስኖ ነበር። ውሳኔውን ተከትሎም የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በዛሬው ዕለት ተከናውኖ ሴራሊዮንን አሸናፊ አድርጓል። ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የአንድ ለዜሮ ድል ብቻ የሚበቃት ሴራሊዮን ኬይ ካማራ በ19ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ነው አሸናፊ የሆነችው። ጊኒ ላይ የተደረገውን ጨዋታ የቤኒን ብሔራዊ ቡድን ብልጫ ወስዶ ቢጫወትም የሚኬል ዱሱዬ ቡድን ግብ ማስቆጠር ሳይችል እጁን ለሴራሊዮን ሰጥቶ ወጥቷል። ውጤቱን ተከትሎም ሴራሊዮን ከ1996 በኋላ ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሷ ተረጋግጧል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሃያ ሁለት ሀገራት ባሳለፍነው መጋቢት ወር በቀጣዩ ዓመት በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሙሉ ለሙሉ ማለፋቸውን ማረጋገጣቸው ይታወሳል።