አዳማ ከተማ ውሳኔ ተላልፎበታል

በሦስት ተጫዋቾች ክስ የቀረበበት አዳማ ከተማ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ እንደተላለፈበት ታውቋል።

በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዡን ግርጌ ይዞ ያጠናቀቀው አዳማ ከተማ የትግራይ ክልል ክለቦች በቀጣይ ዓመት በሊጉ የመኖራቸው ጉዳይ አለመለየቱን ተከትሎ ራሱን በሊጉ ለማቆየት ሰኔ 18 ለሚጀምረው ወሳኝ የአምስት ጨዋታዎች ውድድር ራሱን እያዘጋጀ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ክለቡ በሦስት ተጫዋቾቹ ተከሶ ወሳኔ እንደተላለፈበት ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል። ፍሰሀ ቶማስ፣ ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሔር እና አካሉ አበራ በተባሉት ተጫዋቾች የተከሰሰው ክለቡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ተወስኖበታል።

ሦስቱ ተጫዋቾች በተናጥል መጋቢት 7 ቀን 2013 ለፌዴሬሽኑ ባስገቡት “የመፍትሄ ይሰጠኝ” ደብዳቤ ላይ ክለቡ የተፈራረሙት ውል ሳያልቅ እንዲሰናበቱ መፈለጉን እነሱ ደግሞ በውላቸው መሰረት የ19 ወር ደሞዝ እና የኢንሴንቲቭ ክፍያ ተከፍሏቸው እንደሚለቁ ቢገልፁም ክለቡ የአምስት ወር ደሞዝ ብቻ ለመክፈል ፍቃድ ማሳየቱን አውስተው በዚህ የተነሳ ስምምነት እንዳልመጣ አመላክተዋል። ይሄንን ጉዳይም ሲመረምር የነበረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴም በተጫዋቾቹ እና ክለቡ መካከል የተፈጠረው ክፍተት በግልግል ተመልክቶ መፍታት የሁለቱ ወገኖች መብት መሆኑን ገልፆ ይህ ካልሆነ ግን ተከታዩን ውሳኔ እንዲፈፀም አዟል። በዚህም

– በክለቡና በተጫዋቾቹ ውል አንቀጽ 5 መሠረት ጉዳዩን በስምምነት ለመፍታት ይህ ውሳኔ በደረሳቸው በ4 ቀናት ውስጥ በስምምነት መጨረስ እንዲችሉ ተወስኗል፡፡

– በስምምነት ለመፍታት ካልቻሉ ይህ ውሳኔ ለክለቡ በደረሰው እስከ 7ተኛው ቀን ድረስ ተጫዋቾቹን ወደ ሥራ እንዲመልስ የተቋረጠ ደመወዝ ክለቡ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

– የአዳማ ስፖርት ክለብ ይህ ውሳኔ በደረሰው በ7 ቀናት ውስጥ የተጫዋቾቹን ደመወዝ እንዲከፍል ወይም በውሳኔው መሠረት ተፈጻሚ እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡

– በተባለው ቀንና ሁኔታ ካልፈፀመ ክለቡ በውድድር ተሳታፊ እንዳይሆን እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ተወስኗል፡፡

ከሦስቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ዘሪሁን ብርሃኑ ከተባለው ተጫዋች ጋር በስምምነት ውል እንዳፈረሰ ቀድሞ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የገለፀው ክለቡም ለፌዴሬሽኑ ማስረጃ እንዲያቀርብ መታዘዙ በውሳኔው ተገልጿል።

ፌዴሬሽኑ ሁለቱ አካላት በቅድሚያ እንዲስማሙ በር በከፈተው መሰረትም ተጫዋቾቹ እና የክለቡ አመራሮች ሰኞ ዘጠኝ ሰዓት አዳማ በሚገኘው ሂባ ሆቴል ቢነጋገሩም ስምምነት ላይ ሊደረስ እንዳልቻለ ሰምተናል። ተጫዋቾቹም የዲሲፕሊን ኮሚቴ የወሰነውን ውሳኔ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተፈፃሚ እንዲያደርግላቸው በዛሬው ዕለት ደብዳቤ ማስገባታቸውን አውቀናል።

ይሄንን ጉዳይንም በተመለከተ የክለቡ አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ የአዳማ ከተማ ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንበስ መገርሳ አናግረናቸው ተከታዩን ብለውናል።

“እኛ እንደ አመራር በፊት የተሰሩ ስህተቶችን ለማረም እየጣርን ነው። አዳማ አሁን ያለበት ቦታ አይገባውም። ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ ለሀገር ብዙ የለፋ ክለብ ነው። ይሄንን የክለቡን ገናናነት ለመመለስም እየጣርን ነው። ከሦስቱ ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ ድርድር እያደረግን ነው። ተጫዋቾቹም ሆነ ክለቡ እንዳይጎዱ የሚያደርግ የመጨረሻ ስምምነት ላይም ለመድረስ እየጣርን ነው። ከተጫዋቾቹም ሆነ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር እየተወያየን ነው። ፌዴሬሽኑም እንደ አሸማጋይ ሆኖ ጉዳዩ በቀላሉ እንዲፈታ እንዲያደርግ እየጠየቅን ነው።

“እንደምታቁት አዳማ ከተማ በሊጉ ለመቆየት የሚያስችለውን ውድድር ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው። እንደዚህ አይነት ነገሮችም ክለቡ ላይ መጥፎ ጥላ ያጠላሉ። ይሄ በቶሎ እንዲስተካከልም የተቻለንን እናደርጋለን። ፌዴሬሽኑ የሰጠን የ7 ቀን ገደብም ተጠቅመን ነገ እና ከነገ በስትያ ከፌዴሬሽኑም ሆነ ከተጫዋቾቹ ጋር እንወያያለን።” ብለዋል።

ያጋሩ