የጣና ሞገዶቹ ከአሠልጣኛቸው ጋር ተለያይተዋል

ያለፉትን ሁለት ዓመታት በባህር ዳር ከተማ ያሳለፉት አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በስምምነት ከክለቡ መልቀቃቸው ተገልጿል።

የአሠልጣኝነት ህይወታቸውን በቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሠልጣኝነት የጀመሩት ፋሲል ተካልኝ ከሁለት ዓመታት በፊት የመጀመሪያ የዋና አሠልጣኝነት ህይወታቸውን በባህር ዳር ከተማ ለመጀመር ወደ ጣና ሞገዶቹ ማቅናቱ ይታወሳል። ሐምሌ 10 ቀን 2012 ላይም አሠልጣኙ እና ክለቡ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለመሥራት ዳግም ፊርማ ተፈራርመው የነበረ ቢሆንም ክለቡ ዘንድሮ በተመዘገበው ውጤት ደስተኛ ባለመሆኑ አንድ ዓመት የሚቀረውን ኮንትራት ለማቋረጥ ወስኗል። ከሳምንታት በፊት አሠልጣኙ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት የተመለከተ ሪፖርት እና የቀጣይ ዓመት እቅዶቹን ለክለቡ ቢያስገቡም በሳምንቱ መጨረሻ ከክለቡ የእናናግርህ ጥያቄ ዳግም ቀርቦላቸው ለውይይት ወደ ባህር ዳር አቅንተው ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሠረት አሠልጣኙ ባህር ዳር ሲደርሱ የክለቡ አመራሮች ውሉን በስምምነት ለማቋረጥ እንደሚፈልጉ አስረድተው ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት በሁለቱ አካላት መካከል ሲደረግ ነበር። በውይይቱም አብሮ ለመቀጠል የሚያስችል ስምምነት ሳይደረስ ቀርቶ አሠልጣኙ ከክለቡ እንዲለያዩ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ተደርሷል። እርግጥ አሠልጣኙ የአንድ ዓመት ቀሪ ውል ያላቸው በመሆኑ የኮንትራት ማፍረሻው ጉዳይ አሁንም በድርድር ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።

በ33 ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማ ከአሠልጣኙ ጋር መለያየቱ ከተገለፀ በኋላም ከሁለት አሠልጣኞች ጋር ስሙ እየተያያዘ ይገኛል። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ልዑልም ከፋሲል ጋር ያለው ድርድር ከተቋጨ በኋላ ወደ አዲስ አሠልጣኝ ፍለጋ እንደሚገቡ ነግረውናል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት ሆነው ያገለገሉትና የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ መድን እና መከላከያ ድንቅ ተጫዋች የነበሩት ፋሲል ተካልኝ ደግሞ ከባህር ዳር ጋር ያላቸው ኮንትራት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን ካረጋገጡ በኋላ አሁን እየመጡላቸው ያሉትን የሌሎች ክለቦች ጥያቄዎች እንደሚመለከቱ ሀሳባቸውን ሰጥተውናል።