አዲስ አበባ ስታዲየምን እድሳት ለማድረግ የውል ስምምነት ተካሄደ

አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ለማደስ እና ኢንተርናሽናል ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የውል ስምምነት መካሄዱን የስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል።

እንደ ኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ገለፃ የአዲስአበባ ስታዲየምን በማሳደስ ኢንተርናሽናል ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር ዛሬ የውል ስምምነት ተደርጓል። እድሳቱ በቅድሚያ ካፍ የሰጣቸውን አስተያየቶች መሠረት አድርጎ እንደሚሰራ ሲገለፅ የመጫወቻ ሜዳው፣ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የተመልካች መፀዳጃ እና የኤሌክትሪክ እና የሳኒተሪ ሥራዎችን የሚያካትተውን ጨረታ ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ በ39,644,748.93 ብር ማሸነፉን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ እድሳቱን አጠናቆ ለማስረከብ እንደሚሰራ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ወቅት ገልጿል።

የኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ስታዲየሙ በቀጣይ ዓመት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ጨምሮ በርካታ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑ እድሳቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥራቱን ጠብቆ ሊጠናቀቅ ይገባል ብለዋል። አያይዘውም በሚቀጠለው ዓመት አጋማሽ ላይ ተጠናቆ ለማስረከብ መታቀዱን አያይዘው ገልፀው እድሳቱም በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል ።

የእድሳት ስራውን ዮሐንስ ዓባይ አርክቴክት ኢንጅነሪንግ አማካሪ ድርጅት በቁጥጥር እና በማማከር ይሰራል። የእድሳት ስራው በተሰራው ዲዛይን መሰረት የሚቀጥል ሲሆን በምዕራፍ ሁለት የሚዲያ ክፍሎች ፣ የክብር ትሪቡን መቀመጫ ፣ የወንበር ገጠማ ፣እና ሌሎች የስታዲየሙ ክፍሎችን የማደስ እና ለአገልግሎት ምቹ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል።