ሴካፋ | አምስት ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደረገላቸው

በዛሬው ዕለት ከ28 ተጫዋቾች ሰባቱን በወዳጅነት ጨዋታ የቀነሱት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ጠርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካፍ የልህቀት ማዕከል ማረፊያውን አድርጎ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ ከዝግጅት ጊዜው አስቀድሞ ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው ወደ ሀያ ስምንት ዝቅ ብሎ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዛሬ ረፋድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ብሔራዊ ቡድኑ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ካደረገው የወዳጅነት ጨዋታ በኋላ ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጉዳት እና በጨዋታው ላይ በተመለከቱት እንቅስቃሴ መነሻነት ተጨማሪ ሰባት ተጫዋቾችን እንደቀነሱ በዘገባችን አስታውቀን ነበር፡፡

አሁን ደግሞ በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ከሆነ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾች ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ዓመቱን በሰበታ ከተማ ያሳለፈው እና በአሁኑ ሰዓት ቱርክ የሚገኘው ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ፣ የባህርዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ፂዮን መርዕድ ፣ የሲዳማ ቡናው አማካይ ዳዊት ተፈራ ፣ ከፋሲል ከነማ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው አማካዩ ሀብታሙ ተከስተ እና የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች እና ግብ አግቢው አቡበከር ናስር ለሴካፋ ከ23 ዓመት በታች ቡድን የተጠሩ ተጫዋቾች ሆነዋል።