የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዋቀረው የሎካል ኦርጋናይዚንግ ኮሚቴ ውድድሩ የሚደረግበትን ከተማ ለሁለት ቀን ተመልክቶ መመለሱ ተገልጿል።
ከ1926 ጀምሮ መደረግ የጀመረው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር የ2021 የውድድር ዓመት ፍልሚያው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እንደሚከናወን ይታወቃል። ከሰኔ 26 – ሐምሌ 12 ድረስ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚከናወነው ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በየጊዜው የውድድሩ ቅድመ ዝግጅት እየገመገመ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ከሳምንታት በፊትም የሴካፋ ውድድር ብሔራዊ ዐቢይ ኮሚቴ ከፌደራል መስሪያ ቤቶች ከኢፌዲሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስቴር፣ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም ተዋቅሮ እንደነበር ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የማርኬቲንግ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ ገላጋይ የሴካፋ ዝግጅት Local Organizing Committee ሰብሳቢ ሆነው ተሰይመው በስራቸው 8 ልዩ ልዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ እንደተገባ ይታወቃል። ይሄ ኮሚቴም በትናንትናው ዕለት ወደ ባህር ዳር መጓዙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል።
ትናንት ምሳ ሰዓት ባህር ዳር የደረሰው ልዑኩም ለሁለት ቀን በነበረው ቆይታ ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር የውድድሩ የዝግጅት ሂደትን በተመለከተ ውይይት እንዳደረገ ሰምተናል። በውይይቱም ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከወን ከክልሉ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ምን እንደሚጠበቅ እንደተነጋገሩ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደተቀመጡ በቦታው የነበሩት የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ነግረውናል። ከዚህ ውጪ ኮሚቴው ውድድር የሚደረግበትም የባህር ዳር ስታዲየም እና የልምምድ ሜዳዎች እንደተመለከተ ተገልጿል።
የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል በተጠበቀ ሁኔታ ውስን ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ወደ ሜዳ የሚገቡበትን መንገድ የመከረው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሄደው እና ከክልሉ የተለያዩ ተቋማት የተወጣጣው ኮሚቴም “ደጋፊዎች ወደ ሜዳ መግባት የሚችሉት ሠላም ሚኒስቴር ሲፈቅድ ነው” በሚል ጉዳዩን ወደ ሚመለከተው አካል እንደመሩት ለማወቅ ተችሏል። ፌዴሬሽኑም በቀጣይ ከሠላም ሚኒስቴር ጋር እንደሚወያይ ታውቋል።
በተያያዘ ዜና ውድድሩ በዋናው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንደሚደረግ ቢታወቅም አስፈላጊ በሆነ እና በእኩል ሰዓት መደረግ ባለባቸው የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ግን የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም (ፔዳ ካምፓስ) ግልጋሎት ላይ ሊውል እንደሚችል አቶ ባህሩ አስረድተውናል።