በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መሳተፍ ያልቻለው ስሑል ሽረ በቀጣይ ዓመት ወደ ውድድር ለመመለስ እንቅስቃሴ ጀምሯል።
ከዓመት በፊት በትግራይ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሳተፍ ያልቻሉት መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ በቀጣይ ዓመት በሊጉ የመመለሳቸው ነገር እስካሁን የለየለት መልስ አላገኘም። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም ክለቦቹ ከሐምሌ 1-15 ድረስ በሚኖረው ምዝገባ ከተመዘገቡ እንደሚሳተፉ ካልሆነ ግን በምትካቸው በሌላ አማራጭ ሦስት ክለቦችን እንደሚያሳትፍ ገልፆ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሦስቱ ክለቦች ወደ ሊጉ እንዲመለሱ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑ ሲገለፅ የሰነባበተ ሲሆን አሁን ደግሞ ከሦስቱ ክለቦች ቀድሞ ስሑል ሽረ ወደ ሊጉ የመመለስ ፍንጭ ማሳየቱን ሶከር ኢትዮጵያ ሰምታለች።
2010 ክረምት በተደረገ የመለያ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን ረቶ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ያደገው ስሑል ሽረ አንድ ዓመት ከግማሽ በሊጉ ቆይቶ በኮቪድ-19 እና በፀጥታ ችግር ከሊጉ ርቋል። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በቀጣይ ዓመት ወደ ሊጉ መመለስ የሚያስችለውን ዕድል በመጠቀም እስከ ሐምሌ 15 ድረስ ምዝገባ በማከናወን በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ለመሆን እየጣረ እንደሆነ ሰምተናል። የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ዓለም እንደገለፁልን ከሆነ ክለቡ ወደ ሊጉ የሚመለስበትን መንገድ እየሠራ እንደሆነ ነግረውናል። በዚህም ቡድኑ በያዝነው ሳምንት በቴክኒክ ዳይሬክተሩ በረከት ገብረመድኅን፣ በምክትል አሠልጣኙ መብራቶም ፍስሐ እና በሁለተኛ ቡድን አሠልጣኙ እየተመራ በሽረ እንዳሥላሴ ስታዲየም ልምምድ እንደጀመረ ሥራ አስኪያጁ አውግተውናል።
ልምምድ በጀመረው ቡድን ውስጥ 11 ተጫዋቾች ፕሪምየር ሊጉ ላይ ከተሳተፈው ስብስብ እንዳሉ በተጨማሪም 25 ተጫዋቾች ከሁለተኛ ቡድን (የ”B” ቡድን) እንዲካተቱ ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነ አረጋግጠናል። ምንም እንኳን ከሁለተኛው ቡድኑ 25 ተጫዋቾች ቢኖሩም ወደ ዋናው ቡድን በቋሚነት የሚያድጉት አምስት ተጫዋቾች እንደሆኑም ተነግሮናል።
በተያያዘ ዜና ክለቡ አዲስ ቦርድ ማዋቀሩን እና በቀጣዮቹ ሦስት አልያም አራት ቀናት ስብሰባ እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ዓለም አስረድተውናል።