የአዲስ አበባ ስታዲየም በቀጣይ ዓመት ጨዋታዎችን የማስተናገድ ጉዳይ…

“ስታዲየሙ በቀጣይ ዓመት ውድድር ላይስተናገድበት ይችላል ተብሎ የተነሳው ስጋት ልክ ነው፤ ግን…” አቶ ኤሊያስ ሽኩር

የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትን በተመለከተ እና በቀጣይ ዓመት ስታዲየሙ ውድድር ላያደርግ ይችላል ተብሎ የተነሳውን ስጋት በተመለከተ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ሀሳብ ሰጥተዋል።

ንብረትነቱ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የሆነው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከካፍ በመጡ ገምጋሚዎች ለአህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ብቁ እንዳልሆነ ተገልፆ በካፍ እና ፊፋ እውቅና ያላቸው ጨዋታዎችን እንዳያደርግ መታገዱ ይታወሳል። ስታዲየሙም ጥቅምት 23 1940 የመሰረተ ድንጋይ ተጥሎለት በተለያዩ ጊዜያት የማሻሻያ ግንባታ ተደርጎለት እስከ ዘንድሮ ድረስ የውስጥ እና የውጪ ውድድሮችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንድ ለእናቱ የሆነው የአዲስ አበባ ስታዲየም በጉልህ እድሳት እንደሚያስፈልገው ሲታይ ነበር። ይሄንን የተረዳው የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽንም ስታዲየሙ እንዲታደስ ጨረታ አውጥቶ በዛሬው ዕለት ከተቋራጩ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል። ይሄንን እንቅስቃሴ ተከትሎ የመዲናው አንጋፋ ስታዲየም በቀጣይ ዓመት የሚደረጉ ውድድሮችን ላያስተናግድ ይችላል የሚሉ ሀሳቦች ሲነሱ ነበር። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞም ይሄንን ሀሳብ አንስተው በቀጣይ ዓመት የፕሪምየር ሊጉ ውድድር በአዲስ አበባ የመካሄዱ ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ጠቁመው ማለፋቸው አይዘነጋም። ይሄንን ጉዳይ ተንተርሶም የስታዲየሙ ባለቤት የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር ጥያቄ ቀርቦላቸው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“የአዲስ አበባ ስታዲየም ለበርካታ ዓመታት ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ካፍ ስታዲየሙ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዳይደረጉበት እግድ ጥሏል። እኛ ደግሞ ሌሎቹ የሀገራችን ስታዲየሞች ግንባታቸው ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ቶሎ ለውድድር የሚደርስልን እርሱ እንደሆነ ተረድተን ትኩረታችንን ሰጥተነዋል። ስለዚህ ካፍ በሰጠው ምክረ ሀሳብ መሠረት የስታዲየሙን እድሳት የተመለከተ ጨረታ አውጥተን ስራ ጀምረናል። እርግጥ ጨረታው ሲወጣ ከአንድም ሁለት ጊዜ የመንግስትን አሠራር መከተል ስላለበት ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል። አሁን ግን አሸናፊው ተለይቶ ውል ይዘናል።

“በቅድሚያ የመጫወቻ ሜዳው እንዲቀየር፣ የመልበሻ እና የመታጠቢያ ክፍሎች እንዲሻሻሉ እንዲሁም የተመልካች መፀዳጃ ስፍራዎች በጥራት እንዲሰሩ አስበናል። አሁን ቅድመ ዝግጅት ጨርሰን ወደ ሥራ ገብተናል። ክረምቱን ጀምሮ በ2014 ግማሽ ድረስ ሥራዎች እንዲያልቁ እናደርጋለን።” ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም ስታዲየሙ በቀጣይ ዓመት ውድድር ላያከናውን ይችላል ተብሎ የተነሳው ስጋት እንደ ስጋት ልክ እንደሆነ ገልፀው በታሰበለት ጊዜ ሥራዎችን ለመጨረስ ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

“የአዲስ አበባ ስታዲየም በቀጣይ ዓመት ውድድር ላያደርግ ይችላል ተብሎ የተነሳው ስጋት ልክ ነው። ግን የተለያዩ አማራጮች ይኖራሉ። ቀድሜም እንዳልኩት እድሳቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እናደርጋለን። ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በዙር እንደተከናወነ ይታወቃል። በቀጣይ ዓመትም ይሄ ፎርማት የሚቀጥል ከሆነ የአዲስ አበባ ስታዲየም በዓመቱ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መጨረሻ ያሉ ውድድሮችም እንዲያስተናግድ ሊደረግ ይችላል። ይሄንን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር እንነጋገራለን። ስታዲየሙ ምንም አማራጭ የለውም ፤ መታደስ አለበት። እድሳቱ ደግሞ በጥራት መከናወን አለበት። አሁን የቀረበው ጥያቄ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም ቀርቦልናል። በሚቻለው መንገድ ግን እኛ ግንባታው በታሰበው መንገድ ተጠናቆ በሌሎች አማራጮች ውድድር እንዲደረግበት እናደርጋለን።” ብለዋል።