ጉዞው የተራዘመው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ ወደ እስራኤል ያመራል

በአሠልጣኝ እንድሪያስ ብርሃኑ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከነገ በስትያ ወደ እስራኤል ያቀናል።

ባልተለመደ መልኩ የኢትዮጵያ ወንዶች ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንዲያደርግ እንደታሰበ እና ጨዋታውንም ከሀገር ውጪ ለማከናወን እንደታቀደ እና እግርኳስ ፌዴሬሽኑም የኢትዮጵያ እና የሌሎች ሀገሮችን እግርኳሳዊ ወዳጅነት ለማጠናከር ከበርካታ የአቻ ፌዴሬሽኖች ጋር ግንኙነት እያደረገ እንደሆነ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሀገር ወጥቶ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንዲያደርግ እንዲሁም የልምድ ልውውጦች እንዲኖሩ ከእስራኤል ጋር ውይይት ተደርጎ በጎ ነገሮች ተፈጥረዋል። በዚህም ቡድኑ ሁለት ጨዋታዎችን ወደ ቴል አቪቭ አቅንቶ ለመከወን የፊታችን እሁድ ወደ ስፍራው የሚያመራ ይሆናል።

ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ቴል አቪቭ የሚያመራው ሰኔ 6 እንደሆነ ተገልፆ የነበረ በኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ምክንያት ጉዞው በአንድ ሳምንት እንዲራዘም ሆኗል። በዚህም የፊታችን እሁድ ምሽት 5 ሰዓት 20 ተጫዋቾች፣ 5 የቴክኒክ ብድን አባላት እና 5 አመራሮች በአጠቃላይ 30 የልዑካን ቡድን ወደ ቴል አቪቭ እንደሚያቀና አረጋግጠናል። ቡድኑ ማክሰኞ እና ሐሙስ ሁለት ጨዋታዎችን አድርጎ ሐሙስ ለሊት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በአሠልጣኝ እንድሪያስ የሚመራው ቡድኑ 20 ተጫዋቾችን ይዞ ከአስር ቀናት በፊት ልምምዱን አያት አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል ሲያደርግ ሰንብቷል። ስብስቡ ልምምዱን በሚሰራበት ቦታ (የልዕቀት ማዕከል) መቀመጫውን አድርጎ የነበረ ቢሆንም ከቀናት በፊት ወደ ብሉስካይ ሆቴል ተዘዋውሮ ዝግጅቱን እንደቀጠለ ታውቋል።

ያጋሩ