ከዩንቨርስቲ ውድድሮች ከተገኙ የእግርኳስ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ከሱ ጋር አብረው የተጫወቱ ተጫዋቾች እና አመራሮች ስለ ቁጥብነቱ እና አመለ ሸጋ ፀባዩ ይመሰክሩለታል። የእግርኳስ ሕይወቱን ምንም እንኳን በባህር ዳር ዩንቨርስቲ ቢጀምርም በክለብ ደረጃ አንጋፋው ኤሌክትሪክ የመጀመርያ ክለቡ ነው። በክለቡም አራት ዓመታት ቆይታ አድርጎ በ2010 ወደ ወልዋሎ በማምራት በቢጫዎቹ ቤት ሁለት የውድድር ዓመታት አሳልፏል።
በወልዋሎ በተለይም በመጀመርያ የውድድር ዓመቱ መልካም ጊዜ ያሳለፈው ተጫዋቹ ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት ከደደቢት ጋር በተደረገው ጨዋታ ላይ በደጋፊዎች የሚታወስ ወሳኝ ጎልን አስቆጥሮ ነበር። ጭቃማ ሜዳ ላይ በተደረገው በዛ ጨዋታ ደደቢቶች ሙሉ ብልጫ ወስደው በርካታ ሙከራዎች በማድረግ ለወትሮ ፀጥ የማይለው ሜዳ ድባብን ወደ ጭንቀት ቢቀይሩትም ብልጫ የተወሰደባቸው ባለሜዳዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ በበረከት ተሰማ ግብ ወሳኝ ነጥብ አግኝተው ከመውረድ ተርፈዋል። ዓለምነህ ግርማ ከመዓዝን ያሻማትን ኳስ በግንባሩ ያስቆጠረው በረከትም “በእግር ኳስ ሕይወቴ ካስቆጠርኳቸው ግቦች ምርጧ እና ወሳኟ ናት። ጨዋታው ለኛ በጣም ወሳኝ ነበር። ቡድናችን ላለመውረድ ነበር የሚጫወተው። በዛላይ ብልጫ ተወስዶብን በወሳኝ ሰዓት የተቆጠረኝ ወርቃማ ግብ ነች።” ሲል ስለ ጎሏ ያስታውሳል።
ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ በታሪክ ጥናት የመጀመርያ ዲግሪ ያለውና ቤተሰብ መስርቶ የአንድ ልጅ አባት የሆነው በረከት በሜዳ ላይ ጥሩ መሪ መሆኑ ይነገርለታል። በዚህ ምክንያትም በተጫወተባቸው ሦስቱም ክለቦች በአምበልነት አገልግሏል።
በኮቪድ ምክንያት በተቋረጠው የ2012 የውድድር ዓመት በስሑል ሽረ ከተጫወተ በኋላ የተገባደደው የ2013 የውድድር ዓመትን ክለብ አልባ ሆኖ ያሳለፈው በረከት በወቅታዊ ሁኔታው ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ከእግር ኳስ የራቀበት ምክንያት
ምንም የተለየ ምክንያት የለኝም። መጀመርያ ትግራይ ክልል የተፈጠረው ነገር ብዙ ስፖርተኛ ላይ ጫና ፈጥሯል። አንዱ ክለብ በትንሹ ሀያ አምስት ተጫዋች ይይዛል ብንል በአሁኑ ወቅት ሰባ አምስት ተጫዋቾች በሁኔታው መፈጠር ሥራ አጥ ሆነዋል ማለት ነው። እሱ ነገር መፈጠሩ በኔ ብቻ ሳይሆን በብዙ ተጫዋች ላይ ጫና ፈጥሯል እና አንደኛው ምክንያት እሱ ነው። ሁለተኛ ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከጥሩ ወቅታዊ አቋም ይልቅ ጥሩ መስመር ካለህ ነው ክለብ የምታገኘው። እኔ ደግሞ ብዙም ተግባቢ አደለሁም። እሱ ነገርም ጫና አሳድሮብኛል ብዬ አስባለሁ።
አሁን ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ
አሁንም ከእግር ኳስ አልራቅኩም። በሳምንት አራቴ የግል ልምምድ እሰራለሁ። ከዛ ውጭም የግል ሥራዎች እሰራለሁ። በቀጣይ ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ጠንክሬ በመሥራት ላይ ነኝ። ብዙውን ጊዜዬንም በልምምድ ነው የማሳልፈው።
ባለፈው የውድድር ዓመት ክለብ የማግኘት ዕድል ስለማጋጠሙ
አዎ ከአንዴም ሁለቴ አጋጣሚዎች ነበሩ። ነገር ግን ከቃል ንግግር በዘለለ ይህ ነው የሚባል ነገር አልነበረውም።
በቀጣይ ዓመት ወደ ክለብ እግርኳስ የመመለስ እቅድ
የመጫወት ሙሉ አቅም አለኝ። የፈጣሪ ፍቃድ ከሆነ በቀጣይ ዓመት በአንዱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ እመለሳለሁ። ልምምድም አላቆምኩም ጠንክሬ እየሠራሁ ነው።
ስለ ክለብ ቆይታዎቹ
እግርኳስን በኤሌክትሪክ ኃይል ነው የጀመርኩት። በርግጥ ከዛ በፊት በዩንቨርስቲ ደረጃ ለባህርዳር ዩንቨርስቲ ተጫውቻለው። በኤሌክትሪክ አራት ዓመታት ተጫወትኩ፤ በክለቡ በጣም ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። እንደውም ሁለቱን ዓመት በአምበልነት መርቻለው። ከዛ በ2010 ወደ ወልዋሎ ፈረምኩ። በመጀመርያው ዓመትም ካለ ምንም እረፍት ሙሉውን ጨዋታዎች አደረግኩ ጥሩ ዓመትም ነበር፤ ክለቡን ከመውረድ አትርፈነዋል። በሁለተኛው ዓመት የወልዋሎ ቆይታዬም ጥሩ ነበር፤ ከአንዳንድ ጨዋታዎች ውጭ ተሰልፌ ተጫውቻለው። በ2012 ደግሞ ወደ ስሑል ሽረ ነው የሄድኩት። ሊጉ በኮቪድ ምክንያት ከመቋረጡ በፊት ከተካሄዱት ጨዋታዎች ግማሹን ተጫውቻለው፤ የሽረ ቆይታዬ በከፊል ጥሩ ነበር።
በአምበልነት የመምራት ልምድን ስለማዳበር
በጊዜ ሂደት ራሱ የዳበረ ነገር ነው። አሰልጣኞች በክለቡ ያለህን ተሰሚነት፣ ስነ ምግባር እና የመሪነት አቅም አይተው ነው ለአምበልነት የሚመርጡህ፤ የኔም ተመሳሳይ ይመስለኛል። መጀመርያ በመብራት ኃይል እያለሁ አሰልጣኝ ዮርዳን ስቶይኮቭ ነው አምበል እንድሆን የመረጠኝ። ከዛ በኃላ ብዙ ዓመታት በአምበልነት ተጫውቻለው እና ልምድም አንዱ ምክንያት ነው።