ዋልያዎቹ የሚሳተፉበት የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል መራዘሙን ተከትሎ በቀጣይ መቼ ሊደረግ እንደሚችል ተገልጿል።
ወደ 2022 የተዘዋወረው የካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ 24 የአህጉሪቱን ብሔራዊ ቡድኖች ለማፋለም ቀን እየጠበቀ ይገኛል። ከሦስት ቀን በፊትም በውድድሩ የሚሳተፉት ሁሉም ሀገራት ተለይተው ታውቀዋል። የአፍሪካ እግርኳስ የበላይ የሆነው ካፍ ከጥር 1 እስከ 29 እንደሚደረግ የተገለፀውን ውድድር አራት ቡድኖች ባሉበት በስድስት ምድቦች ከፍሎ እንደሚያከናውን ቢገልፅም የምድብ ድልድሉ እስካሁን አልተደረገም። ከሁለት ሳምንት በፊትም ሰኔ 18 ሊደረግ ታስቦ የነበረውን ድልድል በኮቪድ-19 ምክንያት አስተዳደራዊ ስራዎች ስለዘገዩ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲራዘም ገልፆ ነበር። አሁን በተሰማ መረጃ መሠረት ደግሞ ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ከሀምሌ መጨረሻ እስከ ነሀሴ መጀመሪያ ባሉት ቀናት እንደሚደረግ ተገልጿል።
የካፍ ዋና ፀሃፊ የሆኑት ቬሮን ሞሴንጎ ኦምባ ውድድሩ በሚደረግበት ካሜሩን ርዕሰ መዲና ያውንዴ ሆነው በሰጡት መግለጫ ላይም “የአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ድልድል እስከ ኦገስት አጋማሽ ባሉት ቀናት ይወጣል። ቁርጥ ያለውን ቀን በቅርቡ እንገልፃለን።” ሲሉ ተደምጠዋል። ኃላፊው ጨምረውም ውድድሩ ወደ ሌላ ሀገር ሊዘዋወር ይችላል እየተባለ የሚናፈሰውን ወሬንም አስተባብለዋል። “የአፍሪካ ዋንጫው በጥር ወር እዚሁ ካሜሩን ላይ ነው የሚደረገው።” ካሉ በኋላም ውድድሩ ለየት ያለ መልክ እንዲኖረው በአንድነት መሥራት አለብን የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈው ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።