የአሰግድ ተስፋዬ የመታሰቢያ ውድድር በኢትዮ አፍሪካ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ

በሻላ እግርኳስ ማኅበር አዘጋጅነት ለቀናት በስምንት ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የቆየው የአሰግድ ተስፋዬ የመታሰቢያ ውድድር በኢትዮ አፍሪካ አሸናፊነት ተገባዷል።

የቀድሞ ድንቅ አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ በድንገት ህይወቱ ያለፈበትን አራተኛ ዓመት ለመዘከር በሁለት ምድብ ተከፍሎ ስምንት ቡድን በመያዝ ሃያ ሁለት በሚገኘው አስራ አንድ ቀበሌ ሜዳ በየጨዋታው ቁጥሩ በርካታ የሆነ ተመልካች እየታደመበት ሲዝናና የቆየበት ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ከመዝጊያ ጨዋታ አስቀድሞ ዲጄዎች ከስፖርት ጋዜጠኞች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ በቀጠለው የፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮ አፍሪካን ከአበበ ቢቂላ አገናኝቷል። በዕለቱም የአሰግድ ተስፋዬ ባለቤት ወ/ሮ ገነት በክብር እንግድነት በመታደም ጨዋታውን አስጀምራለች። በዕለቱም አበበ ቢቂላ እግርኳስ ማህበር ለአሰግድ ባለቤት የእርሱ ምስል ያለበት ማስታወሻ ሲበረከትላት በተጨማሪ ለኢትዮ አፍሪካ እና ለሻላ እግርኳስ ማህበር የተለያዩ የአሰግድ ምስሎች ያሉባቸው ስጦታዎች ተሰጥተዋል።

ለፍፃሜው ጨዋታ የሚመጥን በስፍራው ለነበረው ተመልካች አዝናኝ በነበረው በዚህ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ኢትዮ አፍሪካዎች ነበሩ። ጎሉንም የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች እና የደጋፊ ማህበሩ አመራር በመሆን ቡናማዎችን በተለያዩ በጎ ተግባሮቹ ሲያግዝ ምናቀው አብዱራህማን መሀመድ (አቡሸት) ነበር ያስቆጠረው።

በአሰልጣኝ ሳሙኤል ዳኜ የሚመሩት ኢትዮ አፍሪካዎችን በአንበልነት ከመምራቱ ባሻገር ያለውን ከፍተኛ ልምድ በመጠቀም አሁንም አቅም እንዳለው ያስመለከተን ቢንያም ኃይሌ (ዋሴ) የቡድኑ ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች መሆኑን አስመልክቶናል። አበበ ቢቂላዎች በበኩላቸው ጎል ቢቆጠርባቸውም በተመስገን ገብረ ኪዳን አማካኝነት ያገኙትን ዕድል ሳይጠቀሙ ቀርተው ወደ እረፍት መዳረሻው የአቻነት ጎል አስቆጥረዋል። ጎሉንም ጉዙፉ ተጫዋች ዳዊት በሌማ በስሙ አስመዝግቧል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ግለት ቀጥሎ በተለይ በኢትዮ አፍሪካ በኩል አብዱራህማን ሙባረክ ያመከናቸው የጎል አጋጣሚዎች ጨዋታው ወደ መለያ ምት ሳያመራ መጠናቀቅ የሚችሉ አስቆጪ እድሎች ነበሩ።

በአሰልጣኝ ፍሬው ከሚመራው አበበ ቢቂላ ቡድን ውስጥ ሙሉጌታ ሲሳይ እርጋታው፥ የቡድኑን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠርበት መንገድ በብዙዎቹ ተመልካቾች ዘንድ አድናቆትን አትርፏል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው እጅግ ልብን የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል። ይህውም የኢትዮ አፍሪካው አብዱራህማን ሙባረክ እና የአበበ ቢቂላው ግብጠባቂ ሄኖክ መብራቱ በመጋጨታቸው ሄኖክ መብራቱ እግሩ ሊሰበር ችሏል። ይህ አሳዛኝ ጉዳት በተከሰተበት ወቅት በስፍራው የነበሩት የስፖርት ቤተሰቦች እንዲሁም የሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በእንባ የተሞላ ሀዘን ሲያነቡ ተመልክተናል። በስፍራው የነበሩ ግለሰቦች ርብርብ በማድረግ ለተሻለ ህክምና ወደ ሆስፒታል አምርቷል። እጅግ በሚያሳዝነው በዚህ ጉዳት ምክንያት ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ መደበኛው ክፍለ ጊዜ በአንድ አቻ በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው ልማደኛው የኢትዮ አፍሪካው ግብጠባቂ ውብሸት ደሳለኝ ባመከናት ኳስ ኢትዮ አፍሪካዎች 5-4 በማሸነፍ ቻምፒዮን መሆን ችለዋል።

በመጨረሻም ለውድድሩ መሳካት አስተዋፆኦ ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በማስከተል የኮከቦች ሽልማት ለአሸናፊው ቡድን እንዲሁም ለዲጄዎች የዋንጫ እና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቷል።

– ከኮከብ ግብጠባቂ – ውብሸት ደሳለኝ (ኢትዮ አፍሪካ)

– ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – ሚራጅ ነስረዲን (ኢትዮ አፍሪካ በአምስት ጎል)

– ኮከብ ተጫዋች – ቢኒያም ኃይሌ (ኢትዮ አፍሪካ)

– ኮከብ አሰልጣኝ – ሳሙኤል ዳኜ (ኢትዮ አፍሪካ)

– የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ – ኮተቤ እግርኳስ ማኀበር።

ትልቅ አላማ ሰንቆ ለቀናት የተዘጋጀውን ይህን ውድድር በአዘጋጅነት ኃላፊነቱን የተወጣው የኮሚቴ አባላት በጠቅላላ ምስጋና የሚቸረው ሲሆን በተመሳሳይ መሰል የእግርኳሱ ባለውለታዎችን የመዘከር ልማድ እንዲኖር በዚህ አጋጣሚ መጠቆም እንፈልጋለን። ይህን በጎ አላማ በማይወክል ሁኔታ አንዳንድ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ያሳዮት አላስፈላጊ ባህሪ በቀጣይ ውድድሩን እንዳያደበዝዝ መታረም እንዳለበትም እናስገነዝባለን።