በአሠልጣኝ ስታንሊ ኦኩምቢ የሚመራው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለሴካፋ ውድድር የሚያገለግሉትን ተጫዋቾች ጠርቷል።
በአስራ አንዱ የቀጠናው ብሔራዊ ቡድኖች እና በአንድ ተጋባዥ ቡድን (ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ) መካከል የሚደረገው የ2021 የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር ሊጀመር ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል። በውድድሩ ለመሳተፍ ማረጋገጫ የሰጡ ብሔራዊ ቡድኖችም ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ እያቀረቡ ዝግጅታቸውን እየሰሩ ይገኛል። በአሠልጣኝ ስታንሊ ኦኩምቢ የሚመራው የኬንያ ብሔራዊ ቡድንም ከኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመቀጠል ለተጫዋቾቹ ጥሪ አቅርቧል።
ለ32 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረበው ቡድኑ ስም ያላቸው ተጨዋቾችን እንዳካተተ ለማወቅ ተችሏል። ለአብነትም የተስከሩ አጥቂ ሄነሪ ሜጃ፣ በቅርቡ በሲዊድን ሦስተኛ የሊግ እርከን ከሚገኘው ሊንኮፒንግ ሲቲ የውሰት ውሉን አቋርጦ የተመለሰው የጎር ማሂያው ቤንሰን ኦማላ፣ የሊዮፓርዱ ማርቪን ናብዋየር፣ የካርዮባንጊ ሻርክሱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የግብ ዘብ ብርያን ብዋየር እንዲሁም የ19 ዓመቱ የኪሱሙ ኦል-ስታርስ አጥቂ የሆነው እና የናሽናል ሱፐር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (12 ጎል) የሆነው አልፍሬድ ታኑይ በስብስቡ ተካተዋል። የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ስታንሊ ኦኩምቢ የተጫዋቾቹን ስም ይፋ በሚያደርግበት ጊዜም በክለብ ግዳጅ ምክንያት ያልጠራቸው ተጫዋቾች እንዳሉ ገለፆ ባለው ስብስብ ግን ጥሩ ውጤት ኢትዮጵያ ላይ ለማምጣት እንደሚሰሩ አስረድቷል። ሦስት የግብ ዘቦች፣ ዘጠኝ ተከላካዮች፣ አስራ አምስት አማካዮች እና አምስት አጥቂዎች የተካተቱበት የቡድኑ ስብስብ የሚከተለው ነው :-
ግብ ጠባቂዎች
ብርያን ብዋየር (ከካርዮባንጊ ሻርክስ)፣ ካሌብ ኦቲኖ (ከጎር ማሂያ) እንዲሁም ዶልፍ ጁኒየር ኦዊኖ (ከናይሮቢ ስቲማ)
ተከላካዮች
ጂሚ ንዱንጊ (ከተስከር)፣ ፖርቲፈር ኦዲሂአምቦ (ከቪሂጋ ቡሌተትስ)፣ ሲልቬስተር ኦዊኖ (ከካካሜጋ ሆምቦይዝ)፣ ሞሰስ ሙዳቫዲ (ከንዞያ)፣ ኮሊንስ ሺቺንጄ (ከሊዮፓርድስ)፣ ቦኒፌስ ምዋንግሚ (ከካርዮባንጊ ሻርክስ)፣ ዩሱፍ ማይንግ (ከሊዮፓርድስ)፣ ፍሬድሪክ አሉሹላ (ከካርዮባንጊ ሻርክስ) እና ብሪያን ዌፖ (ከኬ ሲ ቢ)
አማካዮች
ጁሹዋ ንያቲኒ (ከፖስታ ሬንጀርስ)፣ ማርቪን ናብዋየር (ከሊዮፓርድስ)፣ ስቬን ይዳህ (ከናይሮቢ ሲቲ ስታርስ)፣ ቪንሰንት ዋሳምቦ (ከኬ ሲ ቢ)፣ ፋራ ኦሚንዴ (ከተስከር)፣ ሬገን ኦቲኖ (ከኬ ሲ ቢ)፣ ኦሊቨር ማሎባ (ከናይሮቢ ሲቲ ስታርስ)፣ ፖተር ቲዮንጎ (ከሊዮፓርድስ)፣ ፍራንሲስ ምዋንጊ (ከምዋታቴ ዩናይትድ)፣ አምብሮስ ሲፉና (ከሶፋፓካ)፣ ጆሴፋት
ሎፓጋ (ከፖስታ ሬንጀርስ)፣ ስታይነር ሙሳሲያ (ከፖስታ ሬንጀርስ)፣ ጆን ንጁጉና (ከኡሊንዚ ስታርስ)፣ ዴኒስ ሙሳማሊ (ከንዞያ ሹገር) እና ኤሊሻ ዌኬሳ (ከንዞያ ሺገር)
አጥቂዎች
ቤንሰን ኦማላ (ከጎር ማሂያ)፣ ሄነሪ ሜጃ (ከተስከር)፣ ሲድኒ ሎካሌ (ከካርዮባንጊ ሻርክስ)፣ ኬን ዋንዮንይ (ከቡንጎማ ሱፐርስታርስ)፣ አልፍሬድ ታኑይ (ከኪሱሙ ኦል-ስታርስ)
ከላይ ስማቸው የተገለፀው ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ተሰባስበው በሀገሪቷ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ መቀመጫቸውን በማድረግ ልምምድ እንደሚሰሩ ተመላክቷል።