የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጊዜ ታውቋል

የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከመቼ እስከ መቼ እንደሆነ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥር የሚገኙ የዘንድሮ ዓመት ውድድሮች እየተገባደዱ (የተጠናቀቁም እንዳለ ልብ ይሏል) እንደሆነ ይታወቃል። በየእርከኑ የሚገኙ ውድድሮች ሲገባደዱም ይፋዊው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከመከፈቱ በፊት ክለቦች ተጫዋቾችን ለማስፈረም ቅድመ ስምምነት እየፈፀሙ እንደሆነ ይሰማል። ይሄ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተጫዋቾች አዲስ ክለብ የሚያገኙበትን የዝውውር መስኮት ቀነ ገደብ መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ ሰምታለች።

በ2014 ለአዲስ ክለብ ለመጫወት የሚያስቡ ተጫዋቾችም የመጀመሪያው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ ከሐምሌ 1 ቀን 2013 (ጁለይ 8/21) እስከ መስከረም 19 ቀን 2014 (ሴፕቴምበር 29/21) ድረስ ተጠቅመው በፌዴሬሽኑ ፊት ህጋዊ እውቅና ያለው ስምምነት እንዲፈፅሙ የ84 ቀን ጊዜ እንደተሰጠ ለማወቅ ተችሏል። በውድድር ዓመት አጋማሽ የሚከፈተው የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ ደግሞ ከየካቲት 28 ቀን 2014 (ማርች 7/22) እስከ መጋቢት 28 ቀን 2014 (ኤፕሪል 6/22) ድረስ እንደሆነ ተገልጿል። በተጠቀሰው ቀነ ገደብም የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ከውጪ ሀገር የሚመጡ ተጫዋቾችም እንደሚስተናገዱ ተጠቁሟል።