የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እስራኤል ይገኛል

ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማድረግ ወደ እስራኤል የተጓዘው ብሔራዊ ቡድኑ በሠላም ስፍራው ላይ መድረሱ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እና እስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ውይይት የተገኘው የሁለቱ ሀገራት ከ17 ዓመት ብሔራዊ ቡድኖች የአቋም መለኪያ ጨዋታ ነገ እና ሀሙስ አመሻሽ እንደሚከናወን መገለፁ ይታወቃል። እነዚህን ጨዋታዎች ለማድረግ ትላንት ለሊት ወደ እስራኤል የተጓዘው የኢትዮጵያ ልዑካንም ለአራት ሰዓት የተጠጋ በረራ ካደረገ በኋላ በሠላም ከማለዳው 12 ሰዓት እስራኤል ገብቷል።

ሠላሳ ልዑካን በመያዝ ከኢትዮጵያ የተነሳው ስብስብም ቴል አቪቭ 12 ሰዓት ከደረሰ በኋላ ከከተማው 30 ኪ.ሜ ወጣ ብላ ወዳለችው ኔታንያ የተባለች ከተማ ማቅናቱ ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመላክታል። አንድ ሰዓት ላይ ኔታንያ ከተማ በሚገኘው ሊዮናርዶ ሆቴል ስብስቡ ከደረሰ በኋላም ቁርስ ተመግቦ እረፍት እንዳደረገ ተጠቁሟል።

ነገ 12 ሰዓት የመጀመሪያ ጨዋታውን ከእስራኤል አቻው ጋር የሚያደርገው ቡድን ውስጥም ምንም የጉዳት እና የህመም ዜና እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል። ከነገው ጨዋታ በኋላ እና ከሀሙስ ሁለተኛ ጨዋታው በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የእስራኤል አቻቸው በቀጣይ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንደሚፈፅሙ ይጠበቃል። በሁለቱ አካላት መካከል የሚደረገው የስምምነት ፊርማም ሀሙስ ረፋድ እንደሚደረግ ተመላክቷል። ሶከር ኢትዮጵያም በጉዳዩ ዙርያ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተለች እንደምታቀርብ መግለፅ ትፈልጋለች።