የአሠልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባጅፋር 0-1 አዳማ ከተማ

በአዳማ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የማሟያ ውድድሩ ጨዋታ በኋካ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

በውድድሩ የተሳተፋችሁበትን ዓላማ አሳክታችኋል። ምን ተሰማህ?

በቅድሚያ ለረዳን አምላካችን ምስጋና እናቀርባለን። የዚህ ውድድር ዕድል ሲመጣ ከአመራሮቹ ጋር የተነጋገርኩት ክለቡን በአንደኝነት እንደማሳልፈው ነው። የተነጋገርኩትን እና የተናገርኩትን በማሳካቴ ደግሞ በጣም ደስ ብሎኛል።

ሲጀምር አዳማ የተበላሸበት ዓምና የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜ ላይ ነው። በተለይ በዝውውር የነበረው ክፍተት ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው። ይህ ነገር አሁንም የሚቀጥል ከሆነ አደጋ ነው። ስለዚህ ከአሁኑ ጀምሮ ስራዎች መሰራት አለባቸው። እንደ አሠልጣኝ ጠንካራ ቡድን መገንባት የምትችለው በዝግጅት ወቅት ነው። እንደተመለከታችሁት አስቸጋሪ ጊዜዎች ነበሩ። ቡድኑንም ለማስተካከል ጊዜዎች ወስደው ነበር። ዞሮ ዞሮ ይሄንንም ዕድል አግኝቶ ተጠቅሟል። ቅድም ይልኩት ነገር ደግሞ ለክለቡ ትልቅ ትምህርት የሚሆነው ነው። እንዳልኩት ግን ትምህርት መሆን አለበት። የሚታወቀው አዳማ ከተማ እንዲመለስ እና በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን ከዛሬ ጀምሮ በዝውውሩ ላይ ስራዎች መከወን አለባቸው። በዚህ አጋጣሚ ይህ መልዕክት ለክለቡ አመራሮች ይድረስ።

በመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ብለው መታየታቸው እና በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው ስለቀረቡበት ምክንያት?

ጅማዎች ይዘውት ወደ ሜዳ የገቡትን አንድ ነጥብ አስጠብቆ ለመውጣት ነበር ሲጥሩ የነበረው። ነጥቡንም እያስጠበቀ ነበር ወደ እኛ ለመሄድ ሲጥር ጠነበረው። እኛም ይሄንን በጥንቃቄ ስንጠብቅ ነበር። እንደዛም ሆኖ እነሱ ጎል እንደርስ ነበር። ግን የመጠቀም ችግር ነበረብን። ማሸነፍ አንደኛ ስለሚያደርገን በሁለተኛው አጋማሽ የአጥቂ ቁጥር በመጨመር ወደ ፊት ለመጫወት ጥረናል። በዚህም ተሳክቶል ግብ አስቆጥረናል።

ከክለቡ ጋር ስላለህ ቆይታ?

ውሌ የሚያልቀው ሐምሌ 30 ነው። ያለውን ነገር በቀጣይ የምናሳውቅ ይሆናል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ተሸንፈው ዓላማቸውን ስለማሳካታቸው…?

ዋና ዓላማችን የነበረው በተገኘው ዕድል በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቆየት ነበር። ይሄንንም ዕድል ተጠቅመናል። በዚህም የጅማን ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በተለይ ደጋፊዎቹ ዓመት ሙሉ በሄድንበት እየደገፉን ከጎናችን አልተለዩም ነበር። የቡድኑንም አመራር በተመሳሳይ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ።

ስለ ጨዋታው?

በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው ጨዋታ ፉክክሩ ጥሩ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ በመውጣቱ የቁጥር ብልጫ ተወስዶብን ነበር። በዚህም የምንፈልገውን ታክቲክ መተግበር ተቸግረናል። አዳማዎች ደግሞ ልምድ ያላቸው ስለሆኑ ጎዶሎነታችንን ተጠቅመውበት ግብ አስቆጥረውብናል።

በተመሳሳጥ ሰዓት ስለተደረገው ጨዋታ…?

የኮልፌ ውጤትን አልጠበቅንም። ጎዶሎ ባንሆን ኖሮ አሸንፈን የምንወጣበት ዕድል ይፈጠር ነበር። በዛሬውም ጨዋታ የራሳችንን ጨዋታ ብቻ ነበር ስንከተል የነበረው። ያኛውን ጨዋታ ተንተርሰን አልተጫወትንም። ወልቂጤ ጠንካራ እንደሆነ እናውቃለን ግን ኮልፌዎች ኳስ ይዘው ስለሚጫወቱ ሜዳው ይመቻቸዋል ብዬ አስቤ ነበር። ዞሮ ዞሮ አቡበከር በቀይ ካርስ እስከሚወጣብን ጊዜ ድረስ ጥሩ ነበርን።

ያጋሩ