የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድናቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እያደረገ ያልሆነበትን ምክንያት አስረድተዋል።
በመስከረም ወር አጋማሽ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ውበቱ አባተ በዛሬው ዕለት ከሰኔ 4 ጀምሮ እያዘጋጁት ስላለው የሴካፋ ቡድን (ከ23 ዓመት በታች) መግለጫ ሰጥተዋል። ከሰዓታት በፊት በተጠናቀቀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ሲነሱ የቆየ ሲሆን እግረ-መንገድ ዋናው ብሔራዊ ቡድን የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ስለማያደርግበት ምክንያት ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ አሠልጣኙ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።
“ልክ ነው። ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ነው የሚገኘው። የእኛ ሀገር መጥፎ ነገር ግን የፊፋ ካለንደር እና የሀገራችን ሊጎች ጊዜ አለመጣጣማቸው ነው። ይሄ ነው ዋናው ችግር እያልኳችሁ ባይሆንም አንደኛው ምክንያት ግን ይሄ ነው። እንደምታቁት የዘንድሮ ፕሪምየር ሊግ ግንቦት 20 ነው የተጠናቀቀው። ከዛ በኋላ ተጫዋቾች ወደየቤታቸው ተበትነዋል። የፊፋ ካሌንደር ደግሞ ከሰኔ መጀመሪያ እስከ አጋማሽ ድረስ ነበር የመጣው። ለዚህ ጊዜ ብለን ተጫዋቾቹን ከቤታቸው መጥራት ደግሞ ብዙም የሚያስኬድ አይደለም። ወይ ለአንድ አልያም ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ተጫዋቾቹን ወደየቤታቸው እንዳይሄዱ ማድረግ ነው። ይሄም ልክ አይመስለኝም።
“አሁን ያለንበት ጊዜ ከክለብ ውድድር ውጪ (Off-season) ነው። ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እኮ ተጫዋቾቻቸውን ከውድድር እየጠሩ ነው የአቋም መለኪያ ጨዋታ የሚያደርጉት። ስለዚህ አንደኛው ችግር የእኛ ሀገር የውስጥ ውድድር እና የፊፋ ካለንደር አለመጣጣሙ ነው። በነገራችን ላይ ከሀገራችን ወጥተን የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንድናደርግ ጥያቄዎች መጥተውልን ነበር። ግን እኛ ሀገር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ማገናዘብ አለብን። እንዳልኩት በውድድር ዝሎ ዓመቱን የጨረሰ ተጫዋች እንደ አዲስ በአንድ ሳምንት ሰብስቦ ጨዋታ ማድረግ ብዙም ውጤት የለውም።”