የስድስቱ ክለቦች ውድድር ዕጣ ወጥቷል

የትግራይ ክልል ክለቦች በ2014 የማይወዳደሩ ከሆነ ለመተካት በሁለተኛው አማራጭ ውድድር ላይ የሚሳተፉት የስድስቱ ክለቦች የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል አመሻሹን ተከናውኗል፡፡

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በትግራይ ክልል በተፈጠረ የፀጥታ ችግር ምክንያት ሦስቱ ክለቦች መሳተፍ ሳይችሉ ቀርተው የተወዳዳሪ ቁጥሩ ቀንሶ በአስራ ሦስት ክለቦች መካከል መደረጉ ይታወሳል፡፡ በቀጣዩ የ2014 የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ላይ ምናልባትም መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ እና ስሑል ሽረ የማይሳተፉ ከሆነ እነሱን ለመተካት በሁለተኛ አማራጭነት የተያዘው ከፕሪምየር ሊጉ የወረዱ ሦስቱ ክለቦች እና ከከፍተኛ ሊግ ከሦስቱ ምድቦች ሁለተኛ ሆነው የጨረሱት ሦስቱ ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ከተያዘለት ሰዓት ከሰላሳ በላይ ደቂቃዎች ዘግይቶ አመሻሹን ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ እና አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እንዲሁም የዚህ ውድድር ጊዜያዊ ሰብሳቢ ሻምበል ሀለፎም ምሩፅ እና ከፌዴሬሽኑ እና ሊግ ካምፓኒው የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ክለቦች እና ሌሎች አካላት በተገኙበት ነው ዕጣው የወጣው።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚደረገው ውድድር ነገ ዓርብ በሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር በወጣው ዕጣ መሠረት 3፡00 ወልቂጤ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር፣ 7፡30 አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ 10፡00 ኮልፌ ቀራኒዮ ከ ሀምበሪቾ ዱራሜ በመክፈቻ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ውድድሩም በየሦስት ቀን ልዩነት ይከናወናል፡፡

በዛሬው የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ላይ የተነሱ ዝርዝር ጉዳዮችን ከቆይታ በኃላ ይዘን እንመለሳለን፡፡