የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ የማይሳተፉ ከሆነ እነርሱን ለመተካት የሚደረገው ውድድር ነገ የሚጀምር ሲሆን የመጀመሪያ ቀን ሦስት ጨዋታዎችንም እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
በዓመቱ መጀመሪያ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት በዘንድሮ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ያልተሳተፉት ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች (መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ) በቀጣይ ዓመት ወደ ሊጉ የመመለሳቸው ነገር የቆረጠለት ምላሽ አላገኘም። የክለቦቹ የተሳትፎ ምላሽ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሊጉን የደረጃ ሠንጠረዥ ግርጌ ይዘው ያጠናቀቁት ወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና አዳማ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ሦስት ምድቦች ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ከጨረሱት ኢትዮ ኤሌክትሪ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ኮልፌ ቀራኒዬ ክ/ከ ጋር የአንድ ዙር የነጥብ ጨዋታ ያከናውናሉ። የዚህ ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓትም አመሻሽ ላይ በሀዋሳ ከተማ ተከናውኗል። በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት ሦስቱንም የነገ ጨዋታዎች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
👉 ጅማ አባጅፋር ከ ወልቂጤ ከተማ (3:00)
በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ መሻሻል እያሳየ ሊጉን የቋጨው ጅማ አባጅፋር የተጫዋቾቹን የደሞዝ ጥያቄ መልሶ ነገ የሚጀመረውን ውድድር ሲጠባበቅ ቆይቷል። ይህ ውድድር ካለቀ በኋላ ዋና አሠልጣኙ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን እንደሚያጣ የታወቀው ጅማ ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥቶ የነገውን ፍልሚያ እንደሚከውን ይታሰባል። በዚህም ቡድኑ ጥቅጥቅ ብሎ በመከላከል እና ኳስን ለተጋጣሚው በመተው ስል የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሊጠቀም እንደሚችል ይገመታል። በዋናነትም የመስመር ተጫዋቹ ተመስገን ደረሰ ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግሮችን በማድረግ ለቡድኑ ጠቀሜታ ለማምጣት እንደሚጥር ይታመናል። ከዚህ አጨዋወት በተጨማሪ ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች ለጅማ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ።
ለዚህ ውድድር አዲስ አሠልጣኝ የሾሙት ወልቂጤ ከተማዎች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሳተፉበት ሊግ ላለመውረድ የመጨረሻ ዕድላቸውን ለመጠቀም ዝግጅት ጨርሰዋል። ኳስን በመቆጣጠር ረገድ ብዙም የማይታማው ወልቂጤ በውድድር ዓመቱ አጋጣሚዎችን ወደ ጎልነት የመቀየር ከፍተኛ ችግር ኖሮበት ታይቷል። ይሄንን ወሳኝ ችግርም አዲሱ አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ለመቅረፍ ስራዎችን ሲሰሩ እንደነበር ተጠቁሟል። ከምንም በላይ በነገው ጨዋታ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች አብዱልከሪም ወርቁ የቡድኑ የግብ ማስቆጠሪያ መነሻ ሆኖ ሊገኝ እንደሚችል ይገመታል። ከእርሱ ከሚነሱት የመሐል ለመሐል ኳሶች በተጨማሪ ፈጣኖቹ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች ቅልጥፍና ለጅማ አደጋን ይዘው ብቅ ሊሉ ይችላሉ።
👉 አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (7:30)
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በድል የጀመረውን ውድድር በማሽቆልቆል ያገባደደው አዳማ ከተማ ከዓመቱ አጋማሽ ጀምሮ አዲስ ቡድን በመገንባት አሳልፏል። በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ በአዳዲስ ተጫዋቾች የተሞላው ስብስብ የተሻለ መናበብ እና በራስ መተማመን ላይ ደርሶም ታይቷል። በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ አመራር ስር የተሰራው ይህ ቡድን የመዋሀድ ምልክት ከሊጉ ባያተርፈውም ነገ በሚጀመረው ውድድር ላይ ግን የተሻለ ጥንካሬን ይዞ ለመምጣት እንደሚያግዘው ይታሰባል። ኳስን ተቆጣጥሮ እስከተጋጣሚ ሳጥን ድረስ ዘልቆ ለመግባት የሚሞክርበት የጨዋታ ሂደትም በተሻለ ሁኔታ ዳብሮ በመክፈቻው ጨዋታ እንደሚታይ ይጠበቃል።
የኳስ ቁጥጥርን መሠረት ባደረገ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሀዋሳ በተካሄደው የሁለተኛው ዙር የምድብ ሀ ጨዋታዎች በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዞ ታይቷል። በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የሚመራው ቡድኑ በሜዳ ላይ ኳስን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት የተሳካ ቢሆንም ወደ ሳጥኑ ጠርዝ ሲደርስ ወጥነት የጎደለው የጎል ማግባት ሂደት ባለማሳየቱ ሲቸገር ተስውሏል። በተለይ በየተሻ ግዛው እና ፀጋ ደርቤ ላይ የተንጠለጠለ የጎል ማግባት ሂደትን መከተሉ እጅጉን ጎድቶት ነበር። በመከላከሉ ሩገድም ፈጣን ሽግግር ለሚከተል ቡድን በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ሆኖ ይታይ ነበር። ሊጉን ለመቀላቀል ሌላ ዕድል ይዞ በመጣው ውድድር ላይም እነዚህን ድክመቶች አሻሽሎ እንደሚመጣ ሲጠበቅ በአማካይ እና በአጥቂ መስመሩ መካከል የነበረው ጥሩ መናበብ ደግሞ ቡድኑ ሊያስቀጥለው የሚገባው ጠንካራ ጎኑ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በጥቅሉ ሁለቱ ተጋጣሚዎች ለኳስ ቁጥጥር የበላይነት ትኩረት ከመስጠታቸው አንፃር በጨዋታው ከፍ ያለ የመሀል ሜዳ ፍልሚያ እንደሚታይበት የሚጠበቅ ይሆናል።
👉 ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ ከ ሀምበሪቾ ዱራሜ (10:00)
በአሠልጣኝ መሐመድኑር ንሃማን የሚመራው እና ከያዘው ስብስበ አንፃር እጅግ አስደማሚ ጉዞ አድርጎ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በታሪክ የመጀመሪያው በፕሪምየር ሊግ የተሳተፈ የክፍለ ከተማ ክለብ (ራሱን ችሎ) ለመሆን ነገ የሚጀምረውን ውድድር ይናፍቃል። በሦስቱም ምድብ ከሚገኙ ክለቦች በተሻለ ኳስን ለመቆጣጠር እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት ያለው ኮልፌ ነገም በዚህ አጨዋወቱ ጨዋታውን ሊቀብር ይችላል። በዋናነትም ኳስን በትዕግስት ከኋላ ጀምሮ በመመስረት የተጋጣሚን ክፍተት ለመፈለግ እንደሚታትር ይታሰባል። በተለይም የመሐል አጥቂው ብሩክን ዒላማ ያደረጉ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች በማዘውተር ግብ ለማስቆጠር ሊታትር ይችላል።
አዲስ አበባ ከተማን ተከትሎ በምድቡ ሁለተኛ ሆኖ የጨረሰው ሀምበሪቾ በአሠልጣኝ ግርማ ታደሠ እየተመራ ጥሩ ዓመት አሳልፎ ነበር። በመከላከሉ ሂደት ጠንካራ የሆነው ሀምበሪቾ በማጥቃቱ ረገድ ግን እምብዛም ተጋጣሚን አስጨናቂ ሆኖ አይታይም። እርግጥ ቡድኑ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርስ እንደ ዳግም በቀለ አይነት ፈጣን ተጫዋቾች ቢጠቀምም አጋጣሚዎችን የመጠቀም ክፍተት ይታይበታል። በአንፃሩ ቢኒያም ተቀይሮ ወደ ሜዳ በሚገባበት ወቅት ያሳይ የነበረው ፈጣን እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ ቡድን ፈታኝ እንደሆነ በተደጋጋሚ ከመታየቱ የተነሳ ነገም የተጫዋቹ መኖር ለኮልፌ ፈተናን ሊሰጥ እንደሚችል ይታሰባል። ከምንም በላይ ግን በፀጋአብ ዮሴፍ የሚመራው የተደራጀው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ነገም ለተጋጣሚ ተጫዋቾች አልቀመስ ሊል እንደሚችል ይታሰባል።