በ2014 የትግራይ ክልል ክለቦች በፕሪምየር ሊግ ካልተሳተፉ በሚል በስድስት ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድር በነገው ዕለት የሚጀመር ሲሆን ዛሬ አመሻሽ በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል የደንብ ውይይቶች፣ አስተያየቶች እና የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት ተደርጓል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክተሩ እና የዚህ ውድድር ሰብሳቢ አቶ ከበደ ወርቁ የተገኙትን ክለቦች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አቶ አበበ ገላጋይ እና ዘሪሁን ቀቀቦ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ አቶ አበበ በንግግራቸው “ይህ ውድድር የተዘጋጀው የትግራይ ክልል ክለቦች ካልመጡ እነሱን ለመተካት የሚደረግ መርሀግብር ነው፡፡ ነገር ግን ክለቦቹ ከመጡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ለሆናቹ ክለቦች እንደ ዝግጅት ተቆጥሮ ወደ ቀጣይ ሊጎቻችሁ የምትመለሱበት ይሆናል።” ብለው በፌዴሬሽኑ አንቀፅ 58 መሠረት የሚደረግ መሆኑን በመጥቀስ ለዚህም ውድድር ደንብ ስለሚያስፈልገው ማቅረያቸውን ተናግረዋል። ፌድሬሽንም ለዚህ ውድድር 60% ወጪ መሸፈኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመቀጠል የዚህ ውድድር ጊዜያዊ ሰብሳቢ የሆኑት ሻምበል ሀለፎም ምሩፅ “ይህን ውድድር የሚመሩ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል። ከሊግ ኮሚቴው እና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተውጣጡ ምሁራን ያሉበት ስብስብ ነው፡፡ በጣም ገለልተኛ ናቸው ያልናቸውንም ነው የመደብነው ብለዋል።
በመቀጠል ከሊግ ኮሚቴው አቶ ዮናስ “ውድድሩ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ይከናወናል። በቀን ሦስት ጨዋታዎችም ይከናወናሉ። ምናልባት የአየር ፀባዩ ከተቀየረ ጨዋታው በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይቀየራል። ደንቡ ላይ የሚስተካከሉ አንዳንድ ነገሮች አሉ። እነሱን አርመን ነገ እንሰጣችኋለን፡፡ ሌላው ውጤታቸው ተቀራራቢ የሆኑ ክለቦች ካሉ የመጨረሻ ጨዋታዎች በተለያየ ሜዳ ይደረጋሉ።” ብለዋል፡፡
በመቀጠል በውድድሩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች አከራካሪ የሆኑ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል። አቶ አበባው ከወልቁጤ “ካልመጡ በሚል ቁርጥ ያለ ነገር ሳይኖር ውድድሩ መደረጉ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ተወዳድረን ነው የምንቀመጠው፤ ከውድድር አንፃር ችግር ሊፈጥርብን ይችላል። ስፖርተኛው ላይም ክፍተት የሚፈጥር በመሆን አስቀድሞ ለምን አልታሰበም?” የመሚህ ጥያቄ ሲያነሱ በመቀጠል ከዛው ከወልቂጤ አቶ ታምራት “በደንቡ አንቀፅ 12 ላይ ዳኛን የሚመድበው የዳኛ ኮሚቴ ሆኖ ሳለ እንዴት የውድድር አመራር ዳኛ ይመድባል? በዚህ አይነት ውድድሩን እንዴት ይከታተላል? የዳኞች ኮሚቴ እያለ ይሄን ለምን ይሆናል?” የሚህ ጥያቄ አንስተው አቶ አበበ ገላጋይ ምላሽ ሲሰጡ “ይሄ ውድድር ለእናንተ የቀረበ ዕድል ነው። ዘንድሮ በተፈጠረ ችግር የክለቦች ቁጥር ወደ አስራ ሦስት ቀንሷል። ቤትኪንግ እና ሊግ ካምፓኒው የተፈራረመው የክለቦች ቁጥር አስራ ስድስት በመሆኑ በ2014 ግዴታ አስራ ስድስት ክለቦች መወዳደር ስላለባቸው የተዘጋጀ አማራጭ ውድድር ነው። አሁንም አስረግጪ የምናገረው የትግራይ ክልል ክለቦች ከመጡ ቀድሞ በተቀመጠው ህግ መሠረት ሊጉን ይቀላቀላሉ። ይሄ ውድድር ለእናንተ የዝግጅት ጨዋታ ይሆናል ማለት ነው። ካልመጡ ግን ተተክታችሁ ትገባላችሁ።” በማለት መልስ የሰጡ ሲሆን የውድድሩ ሰብሳቢ ሻምበል ሀለፎም ከዳኞች ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ “ከዚህ በፊት የዳኞች ኮሚቴ ብቻውን ይወስናል። አሁን ግን በጋራ አወዳዳሪ አካል አብሮ ኮሚሽነርም ጭምር ይመድባል። ይሄ የሚሆነው ግን ዳኞች ኮሚቴ ባቀረበው አካሄድ መሠረት ይሆናል።”ብለዋል፡፡
በመቀጠል ከሀምበሪቾ አቶ ጌዲዮን “አስቀድሞ የጠሩ ነገሮች አለመኖራቸው በደንብ ላይ ክፍተት ሊፈጠር መቻሉን የገለፁ ሲሆን የኤሌክትሪክ ፡ የኮልፌ ቀራኒዮ ክለብ ተወካዮችም ስለ ቅያሬ ተጫዋቾች መጠን፣ የመላቀቅ ስጋት እንዳለባቸው እዚህ ላይ ሀሳብ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዮናስ ሲመልሱ በአጠቃላይ የሚመዘገበው ተጫዋቾች ብዛት 23 ሲሆን በአንቀፅ 14 መሠረትም በደንቡ አምስት ተጫዋች በሦስት ጊዜ ቅያሪ ይደረግባቸዋል፡፡ ቀድሞ የተቋረጠ ጨዋታ ካለ ቀጣዩ ጨዋታ ሰዓቱን ጠብቆ ይደረጋል በማለትም በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
አከራካሪ በነበረው የደንብ ውይይት ላይ አወዳዳሪው አካል ተቀራራቢ ውጤት ያላቸው ቡድኖች ካሉ በተመሳሳይ ሜዳ ጨዋታዎች እንደሚረጉ እና የሚላቀቁ ቡድኖች ካሉ የአምስት መቶ ሺህ ብር ቅጣት እንደሚቀጡ ያብራሩ ሲሆን በመቀጠል እገዳም እንደሚኖረው ከደንቡ ጋር በማያያዝ ተናግረዋል፡፡ በ2013 ቅጣት ያለባቸው ተጫዋቾች በዚህ ውድድር ላይ ቅጣታቸው ተቀባይነት የለውም የተባለ ሲሆን በ2014 ግን ተፈፃሚ ይሆናል ተብሏል፡፡
በስተመጨረሻ የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓቱ ከመካሄዱ በፊት አስቀድሞ ከ1 እስከ 6 የወጣው ቁጥር ተገቢ አይደለም፤ ከአንድ እስከ ሦስት ያሉ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ለምን ሆኑ የሚል አቤቱታ በተለይ ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች በኩል የተነሳ ሲሆን መጨረሻ ላይ ግን በተቀመጠው ቁጥር መሠረት በድምፅ ተመሳሳይ በመሆኑ በኮሚቴው ተለይቶ ዕጣ ሳይወጣ በቀጥታ ወደ ድልድሉ ተኪዶ ዕጣው ከወጣ በኃላ ፍፃሜውን አግኘቷል፡፡